በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የማድሪድ ደርቢ ይጠበቃል።

0
180

ባሕር ዳር: መጋቢት 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ዛሬም ሲቀጥሉ በተለይም የስፔኖቹ አትሌቲኮ ማድሪድ እና ሪያል ማድሪድ በሪያድ ኤር ሜትሮፖሊታኖ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ በጉጉት ተጠባቂ ኾኗል፡፡ ጨዋታው ምሽት 5:00 ላይ ይደረጋል፡፡ በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ሪያል ማድሪድ 2ለ1 ማሸነፉ ይታወቃል።

አትሌቲኮ ማድሪድ እና ሪያል ማድሪድ በቅርብ በተገናኙባቸው 10 ጨዋታዎች አትሌቲኮ ማድሪድ በሁለቱ ብቻ አሸንፏል፡፡ በአንጻሩ ሪያል ማድሪድ በስድስት ጨዋታዎች በማሸነፍ የበላይ ነው፡፡ በሁለት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ የሁለቱ ቡድኖች የድምር ውጤት አሸናፊ በሩብ ፍፃሜው ከአርሰናል እና ፒኤስቪ አሸናፊ ጋር ይገናኛል።

በሌላ ጨዋታ ደግሞ ምሽት 5:00 የእንግሊዙ አርሰናል በኤሚሬትስ ስታዲየም ከፒኤስቪ ጋር ይጫወታሉ፡፡ ሁለቱ ቡድኖች በተገናኙባቸው ዘጠኝ የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች አርሰናል በአራቱ አሸንፏል፡፡ ፒኤስቪ በሁለቱ ድል ነስቷል፡፡ በሦስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ በዘንድሮው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የመጀመሪያው ዙር ጨዋታ አርሰናል 7ለ1 ማሸነፉ ይታወሳል፡፡

በተመሳሳይ ምሽት 5:00 ላይ የእንግሊዙ አስቶንቪላ በሜዳው ቪላ ፓርክ ከቤልጀየሙ ክለብ ብሩዥ ጋር ይጫወታሉ፡፡ ሁለቱ ቡድኖች ከ2024 ወዲህ በሁለት ጨዋታዎች ተገናኝተው ሁለቱም አንዳንድ ጊዜ አሸንፈዋል፡፡ አስቶንቪላ በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ከሜዳቸው ውጭ ክለብ ብሩዥን 3ለ1 ማሸነፋቸው ይታወሳል። የሁለቱ ቡድኖች የድምር ውጤት አሸናፊ በሩብ ፍፃሜው ከፈረንሳዩ ፒኤስጂ ጋር ይገናኛል።

ከወሳኝ ጨዋታዎች ቀደም ብሎም ምሽት 2: 45 ላይ የፈረንሳዩ ሊል የጀርመኑ ቦርሲያ ዶርትሙንድን ይጋብዛል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች በሲግናል ኤዱና ፓርክ ስታዲየም ያደረጉትን የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ አንድ ለአንድ ማጠናቀቃቸው ይታወሳል።

በጥሎ ማለፉ እየተጫወቱ ከሚገኙት 16 ቡድኖች መካከል የጀርመኑ ባየርን ሙኒክ፣ የፈረንሳዩ ፒኤስጂ፣ የስፔኑ ባርሴሎና እና የጣሊያኑ ኢንተር ሚላን ሩብ ፍፃሜውን መቀላቀላቸውን ቢቢሲ ስፖርት እና ዩኢኤፍኤ በድረ ገጻቸው አስነብበዋል፡፡

በሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here