ፋሲል ከነማ እና መቻል የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

0
133

ባሕር ዳር: መጋቢት 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 22ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ሲቀጥል ሦስት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ። ከዛሬዎቹ ጨዋታዎች መካከል ደግሞ ፋሲል ከነማ እና መቻል የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

በ24 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ፋሲል ከነማ ከተከታታይ ሽንፈት በኋላ ነው ዛሬ 9 ሰዓት ሙሉ ነጥብ ለማሳካት የሚጫወቱት። ፋሲል ከተከታታይ ሁለት ድል በኋላ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ሽንፈትን ማስተናገዱ ወጥ አቋም እያሳየ እንዳልኾነ ማሳያ ነው።

ተከታታይ ድል፣ ተከታታይ ሽንፈት እና አቻ ውጤት ያሳየው ፋሲል ከነማ የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ ያሳየው ደካማ እንቅስቃሴ ቡድኑ የአጥቂ መስመሩን መፈተሽ እንዳለበት የሚያሳይ ነው። ከአርባምጭ እና ከባሕርዳር ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ የግብ አጋጣሚዎችን መፍጠር አልቻለም ነበር። ዛሬም ይህን ችግር በመቅረፍ ጨዋታውን ማድረግ ይጠበቅበታል።

ከድል ጋር ከተራራቁ ሰባት የጨዋታ ሳምንታት ያስቆጠሩት መቻሎች በ29 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። መቻል በቅርብ ሳምንታት ከአደረጋቸው ጠዋታዎች መረዳት የሚቻለው የነበረውን የማጥቃት ጥንካሬ ማጣቱን ነው ይህም ቡድኑ ከነበረበት የደረጃ ሠንጠረዡ መሪነት እንዲወርድ አስገድዶታል።

ባለፉት አራት ጨዋታዎች ኳስ እና መረብን ማገናኘት ያልቻለው ቡድኑ ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ቢያገግምም በሁለተኛው ዙር ሁለት ጨዋታ ከአንድ ነጥብ በላይ ማስመዝገብ አለመቻሉ ከፉክክሩ አንድ ርምጃ ወደ ኋላ እንዲቀር አድርጎታል። መቻል በዛሬው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት ከቻለ በደረጃ ሠንጠረዡ አናት ላይ ከተቀመጡት ተከታታይ ክለቦች ጋር ያለውን ልዩነት ዝቅ ማድረግ ይችላል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 14 ጊዜ ተገናኝተው ፋሲል ከነማ ስድስት ጨዋታ በማሸነፍ የበላይነት ሲኖረው መቻል አራት ጨዋታዎች አሸንፏል። ቀሪዎቹ አራት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ነው የተጠናቀቁት። በሊጉ ፋሲል 17 ግቦችን ሲያስቆጥር መቻል 10 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።

በሌላ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከድሬዳዋ 12:00 ሰዓት ይጫወታሉ። አርባ ምንጭ ከመቀለ70 እንደርታ ደግሞ 3:30 ጀምሮ እየተጫወቱ ነው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here