ማንቸስተር ዩናይትድ ዘመናዊ ስታዲየም ሊገነባ ነው።

0
124

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ማንቸስተር ዩናይትድ ከኦልድትራፎርድ በቅርብ ርቀት ላይ በ2 ቢሊዮን ፓውንድ ወጭ ዘመናዊ ስታዲየም ሊገነባ መኾኑን አስታውቋል፡፡ ስታዲየሙ 100ሺህ መቀመጫዎች የሚኖሩት ሲኾን በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ትልቁ ስታዲየም ይኾናል ነው የተባለው።
ስታዲየሙ ሲገነባም ለ92ሺህ ሰዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡

በስታዲየሙ ይዞታ የሚተዳደሩ 17 ሺህ ቤቶችም የሚገነቡ ይኾናሉ፡፡ ቤቶቹ በሀገረ እንግሊዝ የሚደረጉ ስፖርታዊ ጨዋታዎችንም ኾነ ሀገሪቱን ለመጎብኘት የሚመጡ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኝዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያርፉባቸው ይደረጋል፡፡ ይህ ዘመናዊ ስታዲየም መገንባቱ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያስገኛል፡፡

በጠቅላላው ማንቸስተር ዩናይትድ የሚገነባው ዘመናዊ ስታዲየም ለዩናይትድ ኪንግደም ኢኮኖሚ በየዓመቱ 7 ነጥብ 3 ቢሊዮን ፓውንድ ተጨማሪ ገቢ እንደሚያስገኝ ተጠቁሟል፡፡ የማንቸስተር ዩናይትድ የእግር ኳስ ቡድን አሁን እየተጫወተበት የሚገኘው ኦልድትራፎርድ ስታዲየም ተገንብቶ ለጨዋታ ክፍት የኾነው እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በየካቲት ወር 1910 የዛሬ 115 ዓመት ነበር፡፡ 74 ሽህ 197 ተመልካችም የመያዝ አቅምም አለው፡፡

የቀያይ ሰይጣኖቹ አንጡራ ሀብት (ኦልድትራፎርድ) ለረጅም ዓመታት በማገልገሉ ብዙ ነገሮቹ ወደ ኋላ የቀሩ በመኾናቸው መጭውን ጊዜ የሚዋጅ ዘመናዊ ስታዲየም ለመገንባት ወደ ሥራ መገባቱን የክለቡ ባለድርሻ ሰር ጂም ራትክሊፍ መናገራቸውን ቢቢሲ በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡ ግንባታው በአምስት ዓመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሏል።

በሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here