ባሕር ዳር: የካቲት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 28ኛው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ኖቲንግሃም ፎረስት ማንቸስተር ሲቲን የሚጋብዝበት ጨዋታ ከወዲሁ ትኩረትን ስቧል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ የነጥብ ልዩነታቸውም ደግሞ አንድ ብቻ ነው፡፡ በመኾኑም ጨዋታውን አጓጊ አድርጎታል።
ኖቲንግሃም ፎረስት 27 ጨዋታዎችን በማድረግ 14ቱን አሸንፏል፡፡ በስድስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቶ በሰባቱ ደግሞ በመረታት በ48 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በዘንድሮው መርሐ ግብር ”አይሸነፉም” የተባሉትን ቡድኖች በአስደናቂ ሁኔታ እያሸነፈ የመጣው ኖቲንግሃም ፎረስት ዛሬም ማንቸስተር ሲቲን በመርታት የሻምፒዮንስ ሊግ የተሳትፎ ጉዞውን ያደላድላል ሲል ዴይሊ ሜይል ግምቱን አስቀምጧል፡፡
የኖቲንግሃም ፎረስት አሰልጣኝ ኑኖ ኢስፔሪቶ ሳንቶ “ዛሬ የምናደርገው በስመ ጥር አሰልጣኝ ከሚሰለጥን እና ስመ ጥር ተጫዋቾች ካሰባሰበ ቡድን ጋር ቢኾንም ለማሸነፍ እንጫወታለን” ብለዋል፡፡
ማንቸስተር ሲቲ ካደረጋቸው 27 ጨዋታዎች በ14ቱ አሸንፎ፣ በአምስቱ አቻ ተለያይቶ እና በስምንት ጨዋታዎች ተሸንፎ 47 ነጥብ በመያዝ አራተኛ ደረጃን ይዟል፡፡
ኖቲንግሃም ፎረስት ከፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች በሰባቱ ብቻ ሲሸነፍ ማንቸስተር ሲቲ ግን በስምንት ጨዋታዎች ተረትቷል፡፡
የማንቸስተር ሲቲው አሰልጣኝ ጋርዲዮላ “ኖቲንግሃም ፎረስት ዘንድሮ እያሳየ ያለው የአሸናፊነት ስነ ልቦና የሚደነቅ ነው” ብለዋል፡፡ ቡድኑ ያሰባሰባቸው ተጫዋቾችን ችሎታም አድንቀዋል፡፡
ጋርዲዮላ ስለቡድናቸው ወቅታዊ አቋም ”ባለፉት ሰባት ቀናት ውስጥ የቡድናችንን ድክመቶች በመለየት ጥሩ ሥልጠና አድርገናል፡፡ በመኾኑም ዛሬ ተጋጣሚያችን ሊፈትነን እንደሚችል ብናውቅም ማሸነፋችን ግን አይቀርም፤ በአቻ ውጤት መለያየትም አይጎዳንም” ብለዋል፡፡
ስካይ ስፖርት በድረ ገጹ ” ጋርዲዮላ አቻ ውጤትን መፈለጋቸው ‘የእንሸነፋለን’ ፍራታቸው ምልክት ነው” ሲል ጽፏል፡፡
የኾነው ኾኖ ኖቲንግሃም ፎረስት እና ማንቸስተር ሲቲ በቀጣይ ዓመት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ እንዲኾኑ የሚያስችላቸውን ደረጃ ይዞ ለማጠናቀቅ ዛሬ ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ በሰፊው ተጠብቋል፡፡
ጨዋታው ቀን ዘጠኝ ሰዓት ተኩል ይደረጋል፡፡
ሌሎች የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችም ይደረጋሉ፡፡ ምሽት 12 ሰዓት የሊጉ መሪ ሊቨርፑል ወራጅ ቀጣና ላይ የሚገኘውን ሳውዝአምፕተን በአንፊልድ ያስተናግዳል።
በተመሳሳይ ሰዓት ብራይተን ከፉልሃም እንዲኹም ክርስቲያል ፓላስ ከኢፕስዊች ታዎን ይጫወታሉ።
ብሬንትፎርድ ከአስቶንቪላ 2 ሰዓት ተኩል ላይ ይጫወታሉ፡፡ ዎልቭስ ከኤቨርተን ደግሞ ምሽት 5 ሰዓት ላይ የሚገናኙ ይኾናል።
ሊጉን ሊቨርፑል እየመራው ይገኛል፡፡ አርሰናል ሲከተል ኖቲንግሃም ፎረስት በሦስተኛነት ይከተላል፡፡
ኢፕስዊች፣ ሌስተር ሲቲ እና ሳውዝአምፕተን ወራጅ ቀጣና ላይ ይገኛሉ፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን