ስፖርት ሰላምን ለማረጋገጥ እና ማኅበራዊ መስተጋብርን ከፍ ለማድረግ ፋይዳው የጎላ እንደኾነ ተገለጸ።

0
127

ደሴ: የካቲት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ አሥተዳደር ስፖርት ምክር ቤት “ስፖርት ለሰላም እና አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ 26ኛውን ጉባኤ እያካሄደ ነው።

በጉባኤው ላይ የደሴ ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አሕመድ ሙህዬ፣ የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው የሥራ ኀላፊዎች እና ባለ ድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ስፖርት ሰላምን ለማረጋገጥ እና ማኅበራዊ መስተጋብርን ከፍ ለማድረግ ፋይዳው የጎላ እንደኾነ ገልጸዋል።

በቀጣይ በደሴ ከተማ ለሚካሄደው የመላ አማራ ውድድር ከተማ አሥተዳደሩ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ነው የተናገሩት። ይህ ጉባኤ ከውድድሩ በፊት መካሄዱ የተሻለ ዝግጅት ለማድረግ እና በዘርፉ ላይ በጥንካሬ ለመሥራት ያግዛልም ብለዋል።

የደሴ ከተማ አሥተዳደር ወጣት እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ሰይድ አራጋው ጉባኤው የ2016 ዓ.ም ዕቅድ አፈፃፀምን በመገምገም የ2017 ዓ.ም ዕቅድ ትውውቅ እና ኦርንቴሽን ለስፖርቱ ልማት የስፖርታዊ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ብለዋል።

በ2016 በጀት ዓመት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ፕሮጀክቶችን ዕውን በማድረግ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉንም ተጠቁሟል።

የስፖርት ማዘውተሪያዎችን ከማስፋፋት አኳያ የይዞታ ማረጋገጫ እንዲሰጥ መደረጉም በውይይቱ ተነስቷል።

በከተማዋ የቤት ውስጥ ስፖርት ላይ ጥሩ መነቃቃት መኖሩን እና በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚዘጋጁ ውድድሮች ላይ ውጤታማ መኾን መቻሉም ተመላክቷል።

ተሳታፊዎች በቀጣይ የፓራ ሊምፒክ ስፖርት ሠልጣኞችን ያማከሉ እንዲሁም ሌሎች የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን ከተማ አሥተዳደሩ በትኩረት እንዲሠራ ጠይቀዋል።

ዘጋቢ:- ሰልሀዲን ሰይድ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here