ባሕር ዳር: የካቲት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዛሬ 9 ሰዓት ኢትዮጵያ ቡና ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡ ኢትዮጵያ ቡና 18 ጨዋታዎችን በማካሄድ በ29 ነጥብ አራተኛ ደረጃ የሚገኝ ሲኾን ተጋጣሚው ኢትዮ ኤሌክትሪክ እስካሁን 18 ጨዋታዎችን በማካሄድ በ25 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች ዛሬ የሚያደርጉት ግጥሚያ ደረጃቸውን ለማሻሻል የሚያካሂዱት ነው፡፡
ኢትዮጵያ ቡና ባለፈው ከሽሬ እንዳስላሴ ጋር ያደረገውን ጨዋታ 1 ለ 0 ማሽነፍ ቢችልም የነበረው አቋም ግን ዝቅ ብሎ ታይቷል። በተለይም የግብ ክልል ውስጥ ደርሶ ግብ የሚኾኑ ኳሶችን በመፍጠር በኩል ደካማ እንደኾነም ተስተውሏል። በሌላ በኩል ተጋጣሚው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ባለፈው 20ኛ ሳምንት ጨዋታ ከአዳማ ከተማ ጋር ተገናኝቶ የነበረ ሲኾን በጨዋታውም 2 ለ 0 ተሸንፎ ነው የወጣው፡፡
በዚህ ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ቢሸነፍም የተሻለ እንቅስቃሴ ነበረው። በተለይም ወደ ግብ ክልል በመቅረብ ደረጃ የተሻሉ እንደነበሩ ታይቷል፡፡ ወደ ግብ ክልል ቀርቦ ዒላማቸውን የጠበቁ ኳሶችን ሲመቱም ተስተውለዋል፡፡ በሌላ በኩል ሁለቱም ቡድኖች ባለፉት ተከታታይ አምስት ጨዋታዎች ውስጥ አንድ ጊዜ ተሸንፈው አንድ ጊዜ አቻ እና ሦስት ጊዜ የማሸነፍ ታሪክ ያላቸው ናቸው፡፡
ከዚህ አቋማቸው በመነሳት ሁለቱም ቡድኖች ዛሬ የሚያደርጉት ግጥሚያ ተመጣጣኝ ይኾናል ተብሎ ነው የሚጠበቀው፡፡ ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን 16 ጊዜ የመገናኘት አጋጣሚ ነበራቸው። በዚህ ጨዋታም 13 ጊዜ ኢትዮጵያ ቡና እና ሦስት ጊዜ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሲያሸንፉ ሦስት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡
ሌላኛው ጨዋታ 12 ሰዓት ሲቀጥል በደረጃ ሠንጠረዡ በ31 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሀድያ ሆሳዕና በ24 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ሲዳማ ቡና ይገጥማል፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የደረጃ ሠንጠረዥ ኢትዮጵያ መድን በ35 ነጥብ ሲመራ ሀድያ ሆሳዕና በ31 ነጥብ ሁለተኛ እና ባሕርዳር ከተማ ደግሞ በ29 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ተቀምጠዋል፡፡
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!