ፋሲል ከነማ ደረጃውን ለማሻሻል ከአርባ ምንጭ ጋር ይፋለማል።

0
160

ባሕር ዳር: የካቲት 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የ20ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ዛሬ ሲቀጥል አጼዎቹ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር 12 ሰዓት ላይ ይገናኛሉ። አጼዎቹ በ17 ጨዋታ 23 ነጥብ ሰብስበው 12ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ አርባምንጭ ከተማዎች ደግሞ በ17ጨዋታ 24 ነጥብ በመሠብሠብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ሁለቱ ቡድኖች ከአደረጓቸው የቅርብ ጊዜ አምስት ጨዋታዎች ውስጥ ፋሲል ከነማ በባሕርዳር ከተማ 2ለ1 እና በኢትዮጵያ ቡና 1ለ0 ሽንፈት ገጥሞታል። ከመቻል ጋር ያደረገውን ጨዋታ ደግሞ አንድ አቻ ነው የተለያየው። ኢትዮጵያ መድኅንን 1ለ0 እና ድሬደዋ ከተማን 2ለ1 በኾነ ውጤት ማሸነፍም ችሏል።

የዛሬው ተጋጣሚ አርባ ምንጭ ከተማ በበኩሉ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ 2ለ1 ሲሸነፍ ከሀድያ ሆሳህና ጋር ሦስት አቻ እና ከመቀሌ 70 እንደርታ ጋር ሁለት አቻ ተለያይተዋል። ወላይታ ዲቻን 2ለ1 እና ሽሬ እንዳሥላሴን 1ለ0 ማሸነፍ ችለዋል። ሁለቱ ክለቦች ካላቸው ወቅታዊ አቋም ጋር በማነጻጸር የሚያደርጉት የዛሬው ጨዋታ ተመጣጣኝ ሊኾን እንደሚችል ይጠበቃል።

በሌላ በኩል ከዚህ በፊት ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ ስምንት ጊዜ የመገናኘት እድል ነበራቸው። በዚህም ሦስት ጊዜ አጼዎቹ ድል ሲቀናቸው አንድ ጊዜ ደግሞ አርባምንጭ ከተማ ድል ቀንቶታል። አራት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥተዋል። ጨዋታቸውም 12 ሰዓት ይካሄዳል። ሌላው እና ቀደም ብሎ 9 ሰዓት የሚካሄደው ጨዋታ በ17 ጨዋታዎች በ35 ነጥብ የፕሪምየር ሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን እና በ17 ጨዋታዎች 24 ነጥብ በመሰብሰብ 10ኛ ደረጃ ከሚገኘው ወላይታ ዲቻ ጋር የሚካሄደው ጨዋታ ይኾናል።

ሁለቱ ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ አንዱ መሪነቱን ለማጠናከር እና ሌላው ደረጃውን ለማሻሻል የሚካሄድ ነው።

በምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here