ጥራታቸውን የጠበቁ የውድድር እና የልምምድ ሜዳዎች አለመኖር የሊጉ ትልቅ ፈተና መኾኑ ተገለጸ።

0
162

አዲስ አበባ: የካቲት 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ፕሪምዬር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ከሰሞኑ ያደረገውን 6ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ እና በፋይናንስ ተቆጣጣሪ ኮሚቶው በኩል የተወሰዱ እርምጃዎችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል። አክሲዮን ማኅበሩ በ6ኛ መደበኛ ጠቅላለ ጉባኤው ከውድድር ቦታ ችግር፣ ከተመልካች ቁጥር መቀነስ እና አጠቃላይ የውድድር ዓመቱን በተመለከተ የውይይት ሃሳቦችን ማንሳቱን የአክሲዮን ማክበሩ ሥራ አስኪያጅ ክፍሌ ሰይፈ ተናግረዋል።

ጥራታቸውን የጠበቁ የውድድር እና የልምምድ ሜዳዎች አለመኖር የሊጉ ትልቅ ፈተና መኾኑም ገልጸዋል። ውድድሩ በተመረጡ ቦታዎች ብቻ መደረጉ ደግሞ የተመልካች ቁጥር እንዲቀንስ አድርጎታል ነው ያሉት። የክፍያ ሥርዓት መመሪያውን በጣሱ አራት ክለቦች እና 15 ተጫዎቾች ላይ የቅጣት እርምጃ መውሰዱን የገለጸው አክሲዮን ማኅበሩ በተጨማሪ ሁለት ክለቦች እና 10 ተጫዋቾች ላይ ምርመራ እየተደረገ መኾኑም አመላክተዋል።

አክሲዮን ማኅበሩ እርምጃ ሲወስድ በፋይናንስ አሠራር ተቆጣጣሪ ኮሚቴው አስፈላጊውን ማጣራት በማድረግ መኾኑን አንስተዋል። የአክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ የክፍያ ሥርዓት መመሪያው ከመተግበሩ በፊት የክለብ ሥራ አስኪያጆችን ጨምሮ ለሚመለከታቸው አካላት ተደጋጋሚ ሥልጠናዎች እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች መስጠታቸውን ገልፀዋል።

አክሲዮን ማኅበሩ የፋይናንስ መመሪያውን ለመተግበር በትኩረት እንደሚሠራ አፅንኦት የሰጡት መቶ አለቃ ፈቃደ ለእግር ኳሱ ትንሳዔ ሲባል መረር ያሉ ውሳኔዎች ያስፈልጋሉ ብለዋል። አሁን የተወሰደው ቅጣት እና ማጣራት ገና ጅምር መኾኑን እና ተጨማሪ ምርመራዎች እንደሚደረጉም አክሲዮን ማኅበሩ አስታውቋል።

ዘጋቢ፦ ባዘዘው መኮንን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here