የአፄ ፋሲለደስ ስታዲየም የካፍ ደረጃን እንዲያሟላ ተደርጎ ይሠራል” የጎንደር ከተማ አሥተዳደር

0
193

ጎንደር: የካቲት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የአፄ ፋሲለደስ ስታዲየም የዕድሳት ማስጀመሪያ የውይይት መርሐ ግብር በጎንደር ከተማ አካሂዷል። የእድሳት ሥራው ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ወጭ እንደሚጠይቅ የተናገሩት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ማሩ ማሕመድ የእድሳት ሥራው በቅርቡ እንደሚጀመር ተናግረዋል።

ወጪው ከከተማ አሥተዳደሩ በጀት፣ ከአጋር አካላት ድጋፍ እና ከሃብት አፈላላጊ ኮሚቴ በሚሰበሰብ ገቢ ይሸፈናል ያሉት ኀላፊው የእድሳት ሥራው ከስድስት እስከ ስምንት ወር በኾነ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ይሠራል ብለዋል።

የእድሳት ሥራው ተሠርቶ መጠናቀቅ ፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ በሜዳው እንዲጫዎት በር ይከፍታል ያሉት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኛው ሥራውም የካፍ ደረጃን እንዲያሟላ ተደርጎ ይሠራል ነው ያሉት።

ከዋና ስታዲየም እድሳት ባሻገር 5 ትናንሽ የልምምድ ሜዳዎችን እስከ ሰኔ ወር 2017 ዓ.ም ድረስ ተሠርተው እንደሚጠናቀቁም አንስተዋል።

በቅርቡ የሚጀመረው የእድሳት ሥራው በታቀደው ልክ እንዲጠናቀቅ በትብብር መሥራት እንደሚጠበቅ መልዕክት ያስተላለፉት ደግሞ የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ እርዚቅ ኢሳ ናቸው።

የፋሲል ከነማ ደጋፊ ማኅበር አባላት በበኩላቸው የእድሳት ሥራው በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ኀላፊነት እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- አዲስ ዓለማየሁ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here