ዘጠነኛው የመላው ሰሜን ጎንደር ዞን የስፖርት ውድድር ተጀመረ።

0
118

ደባርቅ: የካቲት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዘጠነኛው የመላው ሰሜን ጎንደር ዞን የወረዳ እና ከተማ አሥተዳደሮች የስፖርት ውድድር በደባርቅ ከተማ ተጀምሯል። በውድድሩ በተለያዩ ስፖርት አይነቶች ከ600 በላይ ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉ ይኾናል ተብሏል።

በመርሐ ግብሩ ባሕላዊ እና ዘመናዊ የስፖርት ውድድሮች የሚካሔድ ሲሆን አካል ጉዳተኞችን አካታች የኾነ ውድድር እንደሚካሄድም ተነግሯል። ስፖርት ዓለም አቀፍ ቋንቋ ነው ያሉት የሰሜን ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ቢምረው ካሳ ተወዳዳሪዎቹ እና የስፖርት ቤተሰቡ ስፖርታዊ ጨዋነትን ተላብሰው ውድድሩን ሊያስኬዱ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የሰሜን ጎንደር ዞን ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ መዝናናት ጣዕመ ስፖርታዊ ውድድሩ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እና የአካባቢውን ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል። ኀላፊዋ ስፖርታዊ ውድድሮች ከማዝናናት ባለፈ የእርስ በርስ ግንኙነትን በማጠናከር ወጣቶች እምቅ ስፖርታዊ ችሎታቸውን አውጥተው እንዲያሳዩ ዕድል እንደሚሰጥም ተናግረዋል።

የውድድሩ መክፈቻ የኾነው የደባርቅ ከተማ እና የደባርቅ ወረዳ የወንዶች እግር ኳስ ጨዋታ ባዶ ለባዶ ተጠናቋል። በሌላ ውድድር የአስር ሺህ ሜትር የወንዶች ሩጫ ከደባርቅ ከተማ አትሌት በሪሁን አስማማው አንደኛ፣ከጃናሞራ ወረዳ አትሌት መልካሙ ብርሃን ሁለተኛ ፣ ከጃናሞራ ወረዳ አትሌት መልካም ሰው አለውበል ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

በነገው ዕለትም ዘጠነኛው የመላው ሰሜን ጎንደር ስፖርት ውድድር በተለያዩ መርሐ ግብሮች ቀጥለው እንደሚውሉ ተገልጿል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here