ባሕር ዳር: የካቲት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ25ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐግብር ዛሬ ምሽት 5 ሰዓት ላይ ብራይተን በሜዳው ቸልሲን የሚጋብዝበት ጨዋታ ተጠባቂ ነው፡፡ ቸልሲ እስካሁን ባደረጋቸው 24 ጨዋታዎች በ12ቱ አሸንፏል፡፡ በሰባት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቶ እና በአምስት ጨዋታዎች በመሸነፍ 43 ነጥብ በመያዝ በአራተኛ ደረጃ ይገኛል፡፡
ቸልሲ ምንም እንኳ የዛሬውን ጨዋታ ቢያሸንፍ ነጥቡን ከፍ ያደርገዋል እንጅ የደረጃ ለውጥ አያስገኝለትም፡፡ ብራይተን በበኩሉ ከ24 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው በስምንት ጨዋታዎች ብቻ ነው፡፡ በስድስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቶ በ10 ጨዋታዎች ተሸንፏል፡፡ በ34 ነጥብ እና በሦስት የግብ ዕዳ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
የዛሬው ጨዋታ ለብራይተን ወሳኝ ነው ምክንያቱም ቸልሲን ድል ከነሳው 37 ነጥብ በመያዝ ደረጃውን በሁለት ያሻሽልበታልና ነው፡፡ የጨዋታዎችን ውጤት አስቀድሞ የሚገምተው “ኦፕታ ሱፐር ኮምፒዩተር ” ቼልሲ አሸናፊ ይኾናል ሲል ትንበያውን አስፍሯል፡፡ አቻ ውጤት አትጠብቁም ብሏል፡፡
ጨዋታውን ክሪስ ካቫናኽ በዋና ዳኝነት ይመሩታል፡፡ ሰውየው 16 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን በመዳኘት 83 ቢጫ እና አራት ቀይ ካርዶችን መምዘዛቸውን ዘ ሚረር አስነብቧል፡፡ ሊጉን ሊቨርፑል፣ አርሰናል እና ኖቲንግሃም ፎሬስት በቅደም ተከተል እየመሩት ይገኛሉ፡፡ሌስተር ሲቲ፣ ኢፕስዊች ታውን እና ሳውዝአፕተን ደግሞ ወራጅ ቀጣና ላይ ይገኛሉ፡፡
በሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!