“ስፖርት አንድነታችንን የምናጠናክርበት ሰላማችንንም የምናጸናበት መድረክ ነው” የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር

0
166

ሰቆጣ: የካቲት 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 9ኛው የመላው ዋግ ኽምራ ዘመናዊ ስፖርት ውድድር በጋዝጊብላ ወረዳ አዘጋጅነት በድምቀት ተጀምሯል።

በማስጀመርያ መርሐ ግብሩ መልዕክት ያሥተላለፉት የጋዝጊብላ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ አበባው ደሳለኝ ስፖርት በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘር፣ ቀለም፣ ብሔር ሳይለይ አንድ የማድረግ ኅይል አለው ብለዋል። የመላው ዋግ ኽምራ ዘመናዊ ስፖርት ውድድር ስናካሂድ ወንድማማችነታችንን ልናጠናክርበት ይገባል ነው ያሉት።

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ አብዱራህማን መኮንን የማንነት ጥያቄ ያላቸው የኮረም፣ ዛታ እና ወፍላ ወረዳዎች በድሮው ማንነታቸው መሳተፋቸው ውድድሩን ለየት እንደሚያደርገው ተናግረዋል። በተለይም ስፖርቱን ከሰላም ጋር በማስተሳሰር ማክበራችን ሰላማችንን አጽንተን እንድንቀጥል ያገዛል ነው ያሉት።

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አሥተዳዳሪና የኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ሹመት ጥላሁን ስፖርት አንድነታችንን የሚያጠናክር፣ ሰላማችንን የሚያጸና የሰላም መድረክ ነው ብለዋል። ተወዳዳሪዎች በፍጹም ስፖርታዊ ጨዋነት ውድድራቸውን እንዲያካሂዱ ያሣሰቡት አቶ ሹመት ለሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አሥተዳደሮች መልካም ውጤት እንዲገጥማቸው ተመኝተዋል።

የጋዝጊብላ ወረዳ እና የሰቆጣ ከተማን በእግር ኳስ የወከሉት ይስፋለም ብርሃኑ እና ሞገስ ጌታወይ ለውድድሩ በቂ ዝግጅት እንዳደረጉ ገልጸዋል። ዋንጫውን ለመውሰድ እንደሚወዳደሩ ተናግረዋል።

የመላው ዋግ ኽምራ ዘመናዊ ስፖርት ውድድር በሰባት የስፖርት አይነቶች ከየካቲት 02 እስከ 12/2017 ዓ.ም ድረስ የሚቀጥል ይኾናል።

ዘጋቢ:- ደጀን ታምሩ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here