ደሴ: ጥር 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ሲካሄድ በቆየው የስፖርት ፌስቲቫል ለተሳተፉ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተወካዮች አቀባበል እና የምሥጋና ሽልማት ተካሂዷል። በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተወካይ ፕሬዝዳንት አወል ሰይድ (ዶ.ር)፣ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳደሪ አሊ መኮንን፣ የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ የዩኒቨርሲቲው የሥራ ኀላፊዎች፣ የደሴ ከተማ የንግዱ ማኅበረሰብ ተወካዮች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና በውድድሩ ዩኒቨርሲቲውን የወከሉ ተማሪዎች ተገኝተዋል።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተወካይ ፕሬዝዳንት አወል ሰይድ (ዶ.ር) ልዑካን ቡድኑ ላስመዘገበው ውጤት ምስጋና አቅርበዋል። የዩኒቨርሲቲውን አሸናፊነት አስቀጥላችኋልና ምሥጋና ይገባችኋል ነው ያሉት። ወሎ በእግር ኳስ ስፖርት የሚታወቅ ነው ያሉት ተወካይ ፕሬዝዳንቱ ዩኒቨርሲቲው የእነ ሙሉጌታ ከበደን ታሪክ መድገሙንም ገልጸዋል።ስፖርት ማኅበረሰብን እንደሚያቀራርብም ተናግረዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን ዩኒቨርሲቲውን ወክለው የወሎን ማኅበረሰብ እሴቶች ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻቸው በማሳየታቸው እና አሸናፊ ኾነው አካባቢውን በማስጠራታቸው የልዑካን ቡድኑን አመሥግነዋል። የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ የተገኘው ውጤት የሚያበረታታ መኾኑን ገልጸዋል። ወደፊትም የደሴ ከተማን እና የወሎን ስፖርት ለማሳደግ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲውን ወክለው የተሳተፉ ተማሪዎች ከዓመታት መቋረጥ በኋላ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስፖርት ፌስቲቫል መጀመሩ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል። ስፖርት የትውውቅ እና የወንድማማችነት መድረክ መኾኑንም ተናግረዋል። በማሸነፋቸው እና በተደረገላቸው አቀባበል መደሰታቸውን ተናግረዋል።
ወሎ ዩኒቨርሲቲ በስፖርት ፌስቲቫሉ በእግር ኳስ፣ በባሕል ስፖርቶች፣ በቼዝ፣ በአትሌቲክስ እና በቴኳንዶ በአጠቃላይ በ6 የስፖርት አይነቶች 48 ልዑካንን ማሳተፉ ተገልጿል። በእግር ኳስ እና አትሌቲክስ የወርቅ ሜዳሊያ፣ በቴኳንዶ እና በቡብ የነሃስ ሜዳሊያ ማግኘቱም ታውቋል።
ዘጋቢ፦ከድር አሊ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!