ሰቆጣ: ጥር 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “አካላዊ የስፖርት እንቅስቃሴ ለሚሊዮኖች እና ለአንድነት” በሚል መሪ መልእክት በሰቆጣ ከተማ ፈረስ መጋለብያ ሜዳ ለአንድ ሰዓት ተካሂዷል።
ወጣት ዙፋን ካሴ አካላዊ እንቅስቃሴ ከአሁን በፊት ባለመሥራቷ የሰውነት ክብደቷ በመጨመሩ ለጤንነቷ አስጊ እንደነበረ ገልጻለች።
በቀጣይም ዘወትር ጠዋት አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ጤንነቷን ለመጠበቅ መነሳቷን ወጣቷ አክላ ገልጻለች። አቶ መለሰ ካሣም ከልጃቸው ጋር ሜዳ የተገኙ ሲኾን አካላዊ እንቅስቃሴ የማድረግ ልምድ እንዳላቸውም ተናግረዋል። መሰል ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች መኖራቸው የስፖርቱን ዘርፍ ያነቃቃል ነው ያሉት።
የአካላዊ እንቅስቃሴውን ያዘጋጀው የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሚካኤል ሲሳይ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ከሱሰኝነት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመከላከል አጋዥ ነው ብለዋል።
ለቀጣይም በሳምንት ሦስት ቀን አካላዊ እንቅስቃሴ በከተማ ደረጃ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። ኀላፊው እየተዳከመ ያለውን ዘመናዊ ስፖርት ለማነሳሳትም ያግዛል ብለዋል።
በሰሜኑ ጦርነት የስፖርት ቁሶች እንደወደሙባቸው የገለጹት አቶ ሚካኤል በቀጣይም የታዳጊ ፕሮጀክቶችን በመደገፍና በማገዝ የስፖርቱን ማኅበረሰብ አቀፍ ለማድረግ እንሠራለን ብለዋል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያን በመወከል የተገኙት አቶ አበራ ቢምረው የአካላዊ እንቅስቃሴ ሥራ በሁሉም ወረዳ የሚቀጥል እንደኾነ ገልጸዋል።
ይህን አይነቱ የስፖርታዊ እንቅስቃሴ ደግሞ የተዳከመውን የዞኑን ስፖርት ለማነቃቃትና ለመደገፍ ከፍተኛ እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በዞኑ 20 የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ ቢኖርም የሞተር እና ብስክሌት መለማመጃ ኾነዋል ያሉት አቶ አበራ በቀጣይ ማዘውተሪያ ቦታዎችን በመከለል ለታለመላቸው ግብ እንዲያገለግሉ አበክረው እንደሚሠሩም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!