ባሕር ዳር: ጥር 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሞሮኮ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2025 የሚደረገውን 35ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ታስተናግዳለች፡፡ ውድድሩም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከታኅሣሥ 21 ቀን 2025 እስከ ጥር 18 ቀን 2025 እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡ በውድድሩ 24 ሀገራት ተሳታፊ ይኾናሉ ነው የተባለው። ለወድድሩም አዲስ ዓርማ ከሰሞኑ ይፋ ተደርጓል።
የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጇ ሀገር ሞሮኮ ስድስት ተዋቂ ስታዲየሞችን አድሳ እና የመሠረተ ልማት ማስፋፊያ አድርጋ ማጠናቀቋን አስታውቃለች፡፡ የመጀመሪያው ስታዲየም ”መሐመድ አምስተኛ” ይሰኛል፡፡ ስታዲየሙ ካዛብላንካ ከተማ ውስጥ ይገኛል፡፡ ይህ ስታዲየም የ1988ቱን የአፍሪካ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ በከፍተኛ ድምቀት ማስተናገዱ ይታወሳል፡፡ የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታዎችንም አስተናግዷል፡፡
67 ሺህ ተመልካች የመያዝ አቅምም ያለው ስታዲየሙ በዘመናዊ መልኩ መታደሱ ተገልጿል። እያንዳንዱን ወንበር የሚቆጣጠር ሲስተምም ተተክሎለታል፡፡ በር ላይ የአልኮል መጠጥ የተጎነጨን ሰው ለይቶ የሚያስቀር ቴክኖሎጂም ተገጥሞለታል ነው የተባለው፡፡
”ሙላይ አብደላህ” ሁለተኛው ስታዲየም ነው፡፡ በሞሮኮ ዋና ከተማ ራባት ውስጥ ይገኛል፡፡ 53 ሺህ መቀመጫዎች አሉት፡፡ ስታዲየሙ የፊፋን የክለቦች ዋንጫ እና የሴቶች አፍሪካ ዋንጫን አስተናግዷል፡፡ ሁለንተናዊ እድሳትም ተደርጎለታል። ከፍተኛ መጠን ያለው ኔትዎርክም አለው ተብሏል።
ታንጊር ከተማ የሚገኘው ”የኢባን ባተውታ ስታዲየም” ሦሥተኛው ነው፡፡ 65 ሺህ ተመልካች በወንበር ያስተናግዳል፡፡ የስታዲየሙ ሥነ ሕንፃ ድንቅ ነው። አሁን ላይ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ቅርሶችን በምስል እንዲያሳይ ተድርጓል፡፡
ስታዲየሙ የፊፋ ክለቦችን የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን አስተናግዷል፡፡ የታንጊር ከተማ ደግሞ በጀልባ ለስፔን አንጻራዊ ቅርበት አላት፡፡ ይህ ደግሞ የሞሮኮን ዓለም አቀፍ ትስስር ያጠናክራል ይባላል።
አራተኛው የአድራር ስታዲየም በአጋዲር ከተማ ተገንብቷል፡፡ ይህ ስታዲየም በሀገሪቱ ደቡባዊ የባሕር ጠረፍ አቅራቢያ ይገኛል፡፡ የመንገድ ማሻሻያም ተደርጎለታል፡፡ በኔትዎርክም ተደራሽ እንዲኾን ተደርጓል ተብሏል።
45ሺህ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ያለው ስታዲየሙ የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን ዓለም አቀፍ የወዳጅነት ጨዋታዎችን በተደጋጋሚ ተጫውቶበታል።
”ማራክሽ ስታዲየም” የሀገሪቱ አምስተኛው ስታዲየም ነው። የማራክሽ ከተማ ደግሞ የበርካታ ቅርሶች ባለቤት ናት። ስታዲየሙ እነዚህ ቅርሶች የሚተዋወቁበት ሰፋፊ ስክሪኖችን እንዲይዝ የተደረገ ስታዲየምም ነው፡፡
45ሺህ 240 ተመልካች የመያዝ አቅም ያለው የማራክሽ ስታዲየም ከዚህ ቀደም የፊፋን የዓለም ክለቦች ዋንጫ ጨዋታዎችን አስተናግዷል። ማራክሽ ፈጣን የባቡር ኔትወርክ ተደራሽ የኾነባት ከተማ ስለመኾኗም ይነገራል።
የ”ዲ ፌስ” ስታዲየም ስድስተኛው ሲኾን በጥንታዊዋ የፋዝ ከተማ ይገኛል፡፡ ስታዲየሙ እስከ 35ሺህ ተመልካቾችን ማስተናገድ የሚችል ነው፡፡ እነዚህን ጨምሮ ዘጠኝ ስታድየሞች በስድስት ከተሞች ተዘጋጅተዋል። ውድድሮችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ቅንጡ ሆቴሎች፣ መዝናኛዎች እና የትራንስፖርት አውታሮችም ተገንብተውለታል ነው የተባለው፡፡
ስታዲየሞች በሚገኙባቸው ከተሞች የመብራት መቆራረጥ እንዳይኖር ከሐይድሮ ኤሌክትሪክ በተጨማሪ የሶላር እና የዲዝል ኀይል ተሟልቶላቸዋል፡፡
በሚገኙባቸው ቅንጡ ሆቴሎች፣ የትራንስፖርት፣ የስልክ፣ የመዝናኛ፣ የመገናኛ፣ የደኅንነት መቆጣጠሪያ ዘዴዎች፣ ሁሉን አቀፍ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እና እድሳት እንደተደረገላቸው ነው ካፍ ኦን ላይን ኒውስ ያስነበበው፡፡
ሞሮኮ የአፍሪካ ዋንጫን በማስተናገድ ረገድ በሁሉም መመዘኛ ድንቅ ለማድረግ ተዘጋጅታለች ነው የተባለው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!