አርሰናል እና ሊቨርፑል ከተጋጣሚዎቻቸው ጋር ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

0
201

ባሕር ዳር: ጥር 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ 22ኛ ሳምንት ዛሬ አምስት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ። ከእነዚህ ጨዋታዎች መካከል የደረጃ ሠንጠረዡ መሪ ሊቨርፑል እና በቅርብ ርቀት እየተከተለው የሚገኘው አርሰናል ሁለቱም በየፊናቸው ከተጋጣሚዎቻቸው ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

47 ነጥብ በመሠብሠብ ደረጃውን እየመራ የሚገኘው ሊቨርፑል ወደ ብሬንትፎርድ ተጉዞ በ28 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ካለው ተጋጣሚው ጋር ነው ጨዋታውን የሚያከናውነው።

ሁለቱ ቡድኖች ከጎል ማግባት አኳያ ሲታዩ የተሻሉ ሲኾኑ ሊቨርፑል በፕሪምርሊጉ በእስካሁኑ ጉዞ 48 ግቦችን በተጋጣሚዎቹ መረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል።

በሌላ በኩል ብሬንትፎርድም ወደ ተጋጣሚው የጎል ክልል ደርሶ ጎል በማስቆጠር ችግር የለለበት ክለብ ነው። በዚህ የውድድር ዘመን 40 ግቦችን በተጋጣሚዎቹ መረብ ላይ ማግባት የቻለ ክለብ ነው።

ሊቨርፑል ያለውን ወቅታዊ አቋም ስንመለከት በዘንድሮው ዓመት ማንም አያቆመውም ተብሎ የነበረ ቢኾንም አሁን ላይ ግን እየተፈተነ ይገኛል። በቅርብ ጨዋታዎች በፕሪምሪሊጉ ከኖቲንግሀም ፎረስት ጋር አንድ አቻ ሲለያይ በኤፍኤ ካፕ ጨዋታ አክሊንግቶን ስተንለይን 4ለ0 አሸንፏል፣ በቶትንሀም ሆትስፐር ደግሞ 1ለ0 ተሸንፏል፣ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ሁለት አቻ ሲለያይ ዌስትሀምን 5ለ0 ማሸነፍ ችሏል ይህም ቡድኑ ወጥ አቋም እንደሌለው የሚያሳይ ነው።

በሌላ በኩል ተጋጣሚው ብሬንትፎርድም ከማንቸስተር ሲቲ ጋር 2ለ2 ሲለያይ በኤፍኤ ካፑ በፕለይማውዝን 1ለ0 የተሸነፈ ቡድን ነው፣ ሳውዝ አምፕተንን 5ለ0 ያሸነፈው ቡድኑ በአርሰናል 3ለ1ተሸንፏል፣ከብራይተን ጋር ደግሞ ያለግብ ተለያይቷል።

ሁለቱ ቡድኖች 17 ጊዜ ተገናኝተው ዘጠኝ ጊዜ ሊቨርፑል አራት ጊዜ ብሬንትፎርድ ሲረቱ አራት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ሊቨርፑል በሰው ሜዳ የሚጫዎት ቢኾንም በቅርብ ከዚሁ ቡድን ጋር ያደረጋቸውን ሦስት ጨዋታዎች ያሸነፈ በመኾኑ የማሸነፍ ግምቱን ግን አግኝቷል። ጨዋታውም ምሽት 12:00 ይደረጋል።

ሌላው ተጠባቂ ጨዋታ በኤምሬትስ ስታዲየም አርሰናል ከአስቶንቪላ የሚያደርጉት ጨዋታ ነው። በ43 ነጥብ 2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርሰናል በ35 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው አስቶንቪላ ጋር ነው ጨዋታውን የሚያደርገው።

አርሰናል በፕሪምየርሊጉ የእስካሁኑ ጉዞ 41 ኳሶችን ከመረብ አሳርፏል፤ ተጋጣሚው አስቶንቪላ በበኩሉ 31 ኳሶችን ነው ወደ መረብ መጨመር የቻለው። አርሰናል በቅርቡ የማሸነፍ ስነ ልቦናው ቶትንሀም ሆትስፐርን 2ለ1 በማሸነፍ ቢመለስም ከዚህ ጨዋታ ቀደም ብሎ በኤፍ ኤ ካፕ በማንቸስተር ዩናይትድ ሲሸነፍ፣ ኒውካስትል ዩናይትድም 2ለ0 አሸንፎታል፣ ከብራይተን ጋር 1ለ1 የተለያየው ቡድኑ ብሬንት ፎርድን 3ለ1 ማሸነፍ ችሏል።

በሌላ በኩል ተጋጣሚው አስቶንቪላ በፕሪምርሊጉ በኒው ካስትል ዩናይትድ 3ለ0 ከመሸነፉ እና በብራይተን ሁለት አቻ ከመለያየቱ በቀር ኤቨርተንን 1ለ0፣ ዌስትሀምን 2ለ1፤ ሌሰስተር ሲቲን 2ለ1 በመርታት ጥሩ አቋም ያለው ቡድን ነው።

ሁለቱ ቡድኖች 187 ጊዜ ተገናኝተው 82 ጊዜ አርሰናል ሲያሸንፍ 66 ጊዜ ደግሞ አስቶንቪላ አሸንፏል፤ ቀሪው 39 ጊዜ ደግሞ አቻ የተለያዩበት ጨዋታ ነው።

የዛሬውን ጨዋታ ከማሸነፍ ቅድመ ግምት አኳያ አርሰናል በሜዳው በመጫወቱ እና በቅርብ ሁለቱ ቡድኖች ካደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች ሁለቱን አርሰናል በማሸነፉ ቅድመ ግምቱን ወስዷል። ጨዋታውም ምሽት 2:30 ይካሄዳል።

በእንግሊዝ ፕሪምርሊግ ሌሎች ጨዋታዎችም ሲቀጥሉ ቀን 9:30 ኒውካስል ዩናይትድ ከበርንማውዝ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፤ ሌስተር ሲቲ ከ ፉልሃም፤ ዌስትሃም ዩናይትድ ከክሪስታል ፓላስ የሚያደርጉት ጨዋታ ደግሞ ምሽት 12:00 እንደሚካሄድ ይጠበቃል።

በምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here