ባሕር ዳር: ጥር 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአደይ አበባ ስታድየም ግንባታ ፕሮጀክት አፈጻጸም ተስፋ ሰጭ መኾኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ የማኅበራዊ ልማት፣ የባሕል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገልጸዋል። ቋሚ ኮሚቴው በአዲስ አበባ ከተማ በቻይና ኮንስትራክሽን ኮሙኒኬሽን ካምፓኒ አማካኝነት በ57 ሚሊዮን ዶላር እየተገነባ ያለውን የአደይ አበባ ብሔራዊ ስታድየም ያለበትን ደረጃ ተመልክቷል።
ከተጀመረ ከ10 ዓመት በላይ ያስቆጠረው የአደይ አበባ ስታድዮም ግንባታ ፕሮጀክት የኢፌዴሪ ባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ጋር በወሰደው የማስተካከያ እርምጃ አሁን ያለበት አፈጻጸም እና የሥራ እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጭ ነው ተብሏል። ለበለጠ ፍጥነት ክትትሉ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ያሉት ደግሞ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወርቀሰሙ ማሞ ናቸው።
አሁን ያለው የፕሮጀክቱ አፈጻጸም የአመራር ቁርጠኝነት የታየበት ነው ብለዋል ሰብሳቢዋ። የኢትዮጵያ ሕዝብ በናፍቆት የሚጠብቀው ስታድየሙ ዓለም ዓቀፍ እስታንዳርዱን ጠብቆ የሚገንባ እስከኾነ ድረስ የሀገር ገጽታን የመገንባት ድርሻው ከፍተኛ በመኾኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሰቢ ታደለ ቡራቃ(ዶ.ር) ቀደም ሲል የነበረው የፕሮጀክቱ ተስፋ አስቆራጭ ታሪክ በመቀየሩ መደሰታቸውን ተናግረዋል። እንደዚህ ያለ ትልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት ለአንድ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ብቻ የሚተው ሳይኾን የሁሉንም አካላት ትኩረት የሚፈልግ እንደኾነ እና ቋሚ ኮሚቴውም የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላትም በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ይሁን እንደመንግሥት የተወሰደው የማስተካከያ እርምጃ ሕዝብ እና መንግሥትን የሚያቀራርብ ብቻ ሳይኾን ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስኬት በመኾኑም አመራሩ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል።
የኢፌዲሪ ባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ የአደይ አበባ ስታዲዮም ግንባታ ፕሮጀክት ቁልፍ ችግሩ ተለይቶ እየተሠራ ያለ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በ2029 የአፍሪካ ዋንጫን ማዘጋጀት እንዳለባት ግብ ተቀምጦ እየተሠራ በመኾኑ የተጀመረው ክትትል እና ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!