የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሳምንታት በኋላ ዛሬ ጨዋታዎችን ያካሂዳል።

0
180

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለ11 ሳምንታት በድሬዳዋ ሲከናወን ቆይቷል። ከሁለት ሳምንታት ቆይታ በኋላ ዛሬ ሊጉ ሲመለስ ጨዋታዎች አዳማ ላይ ይካሄዳሉ። ዛሬም ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ፋሲል ከነማ ከሀዋሳ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ ደግሞ ትኩረት አግኝቷል። አጼዎቹ በደረጃ ሰንጠረዡ 14 ነጥቦችን በመያዝ ዘጠነኛ ናቸው። የአሠልጣኝ ውበቱ አባተ ቡድን ድሬዳዋ ላይ በተጠበቀው ልክ ውጤታማ አልነበረም። ነገር ግን በመጨረሻ ሦሥት ጨዋታዎች በጥሩ መነቃቃት ላይ ታይቷል።

ተከታታይ ድሎችን አስመዝግቦ መምጣቱም በእንቅስቃሴ ደረጃ የተሻለ ኾኖ ለሚታየው ፋሲል ለዛሬው ጨዋታ ስንቅ ይኾናል። አጀማመሩ መልካም የነበረው ሀዋሳ ከተማም የድሬዳዋ ቆይታው ጥሩ የሚባል አይደለም። ቡድኑ ዘጠኝ ነጥብ ብቻ በድሬዳዋ ቆይታው አሳክቷል።

በቅርብ ካደረጋቸው ስድስት የሊግ ጨዋታዎች ማግኘት የቻለው ሁለት ብቻ መኾኑን የሶከር ኢትዮጵያ ዘገባ ያሳያል። ይህም ቡድኑ ምን ያህል በውጤት ማሽቆልቆል ውስጥ አንደሚገኝ ማሳያ ነው። ይህም ከአሠልጣኝ ዘርአይ ሙሉ ጋር እንዲለያዩ ምክንያት ኾኗል።

በሁለቱ ክለቦች የእስካሁን ግንኙነት አምስት ጊዜ አጼዎቹ አሸንፈዋል። አራቱን ሀዋሳዎች ሲረቱ በቀሪ ስድስት የጨዋታ ግንኙነታቸው ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። ጨዋታው ምሽት 12:00 ሰዓት ይጀምራል።

ከዚህ ጨዋታ ቀደም ብሎ አርባ ምንጭ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ይጫወታሉ። ተመሳሳይ አስራ ሦሥት ነጠብ በመያዝ በግብ ክፍያ የተበላለጡት ሁለቱ ቡድኖች 9:00 ሰዓት ጀምረው ይጫወታሉ።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here