ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጉዳት የበረታባቸው ክለቦች፣ በተጫዋቾቻቸው ደስተኛ ያልኾኑ አሠልጣኞች ክፍተቱን ለመሙላት የጥር የተጫዋቾች ዝውውርን ይጠቀሙበታል። በተመሳሳይ በየክለቦቻቸው ተገቢው የመጫወት ዕድል አላገኘንም ብለው የሚያስቡ ተጫዋቾችም ይህን የዝውውር ጊዜ አዲስ ክለብ ለማግኘት ይጠቀሙበታል።
በተለይ ከአሠልጣኞቻቸው ጋር ለተኳረፉ ተጫዋቾች እንደመፍትሄ መፈለጊያ መንገድ ይቆጠራል። ይህ ዛሬ የተጀመረው የጥር የተጫዋቾች የዝውውር ጊዜ እንደ አውሮፖውያኑ ቀን እስከ የካቲት ሦስት ድረስ ይቆያል። በእነዚህ ጊዜያትም የሚጠበቁ ዝውውሮች አሉ ሲል ቢቢሲ በስፖርት ገጹ ጽፏል።
ቀዳሚው ጉዳይ ደግሞ የሊቨርፑሉ አሌክሳንደር አርኖልድ ጉዳይ ነው። ይህ የቀኝ ተመላላሽ በሊቨርፑል የስድስት ወር ውል ብቻ ይቀረዋል። ረያልማድሪድ ደግሞ ተጫዋቹን ለማስፈረም በአንድ እግሩ ቆሟል። እንደዘገባዎች ከኾነም አርኖልድ ሪያልማድሪድን የመቀላቀል ፍላጎቱ ከፍ ያለ ነው። ጥያቄው ግን ሊቨርፑል ተጫዋቹን በዚህ ወር ለስፔኑ ክለብ ይሸጣል ወይስ በሰኔ ከክለቡ በነጻ ይወጣል የሚለው ነው? የጥሩ የዝውውር ገበያም ለዚህ ምላሽ ይሠጣል።
የማርከስ ራሽፎርድ ጉዳይ ሌላኛው በዚህ ዝውውር የሚጠበቅ ጉዳይ ነው። ተጫዋቹ በአሠልጣኝ አሞሪም ፊት እንደተነሳው በተደጋጋሚ ታይቷል። ይህን ተከትሎ ራሽፎርድ ለአዲስ ፈተና ዝግጁ መኾኑን መግለጹ ይታወሳል። ተጫዋቹ በፒኤስጅ፣ በባርሴሎና እና በሳዑዲ ክለቦች እየተፈለገ ይገኛል።
ጥንካሬው የከዳው ማንቸስተር ሲቲ በዚህ የዝውውር ጊዜ መፍትሄ ፍለጋ የሚሄድበት ርቀትም ይጠበቃል። በዋናነት ማርቲን ዙምቢመንዲን ከሪያል ሶሴዳድ ለማስፈረም ጥረት ጀምሯል። ስፔናዊ አማካይ በሮድሪ ጉዳት የፈረሰውን የሲቲን አማካይ ክፍል እንዲጠግን ይፈለጋል።
በተጨማሪም የተከላካይ ክፍል እና የአጥቂ ተጫዋች ፍለጋ ወደ ገበያው እንደሚወጣ ይጠበቃል። እንግሊዛዊው ቢን ችልዌል በቸልሲ እንደማይፈለግ በኢንዞ ማሬስካ የተነገረው ተጫዋች ነው። ተጫዋቹ በክረምቱ የተጫዋቾች ዝውውር ጊዜ ከቼልሲ እንደሚወጣ ተጠብቆም ነበር።
በአሠልጣኙ ማሬስካም የመሰለፍ ዕድል አላገኘም። በዚህ ዝውውር አዲስ ክለብ እንደሚቀላቀል ይጠበቃል። ጁቬንቱስ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ እና ብሬንትፎርድን የመሳሰሉ ክለቦችም የተጫዋቹ ፈላጊዎች ናቸው።
በወልቭስ ቤት ጥሩ ጊዜን እያሳለፈ ያለው ማቲያስ ኩኛ በትልልቅ ክለቦች እየተፈለገ ነው። በተለይ በሳካ ጉዳት ምክንያት አርሰናል ብራዚላዊውን ተጫዋች ለማስፈረም ፍላጎቱ ከፍ ብሏል።
ከአርሰናል በተጨማሪ ሊቨርፑል፣ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ማንቸስተር ሲቲ እና ኒውካስትል ዩናይትድ ኩኛን ለማስፈረም ፍላጎት አላቸው።
ተጫዋቹ የትኛውን ክለብ ይቀላቀላል? ወይስ ላለመውረድ የሚጫወተው ወልቭስ ብራዚላዊውን ያቆያል የሚለውም በዚህ የዝውውር ጊዜ የሚጠበቅ ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!