የባሕል ስፖርቶች ለሰላም ግንባታ ወሳኝ ሚና አላቸው።

0
128

ጎንደር: ታኅሣሥ 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 22ኛው የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የባሕል ስፖርቶች ውድድር እና 18ኛው የባሕል ስፖርቶች ፌስቲቫል በላይ አርማጭሆ ወረዳ ትክል ድንጋይ ከተማ ተጀምሯል። በውድድሩ በዞኑ ከሚገኙ ሰባት ወረዳዎች የተወጣጡ የባሕል ስፖርት ተወዳዳሪዎች የተሳተፉ ነው። ትግል፣ ገበጣ እና መሰል የባሕል ስፖርት ዘርፎች ናቸው በውድድሩ የሚቀርቡት።

የባሕል ስፖርት ፌስቲቫሉ የዞኑን ባሕል እና እሴት ከማጎልበት ባሻገር የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር እና መቀራረብን በመፍጠር ለሰላም ግንባታ የራሱ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ድግስ መለስ ገልጸዋል። “የሚካሔደው የባሕል ስፖርት አንድነታችንን እና አብሮነታችንን የምናንጸባርቅበት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

የባሕል ስፖርት ፌስቲቫሉ የትክል ድንጋይ ከተማን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚያነቃቃ መኾኑን የተናገሩት ደግሞ የላይ አርማጭሆ ወረዳ ምክትል አሥተዳዳሪ አስረሳው ደሴ ናቸው።

አቶ አስረሳው ስፖርት ዘር፣ ቀለም፣ ሃይማኖት የማይለይ መኾኑን አንስተው ሰላማዊ እና ስፖርታዊ ፋክክር እንዲያደርጉ ለተወዳዳሪዎች መልዕክት አስተላልፈዋል።

የባሕል ስፖርት ፌስቲቫሉ እስከ ታኅሣሥ 28/2017 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ይኾናል።

ዘጋቢ:- ተስፋዬ አይጠገብ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here