ለእግር ኳሱ ሰበብ እስከ መቼ!?

0
430

የአፍሪካን እግር ኳስ ባለውለታ ኢትዮጵያ በአፓርታይድ ምክንያት በምሥረታው ወቅት በመድረኩ ካልተሳተፈችው ደቡብ አፍሪካም ኾነ፣ ከግብጽ እና ከሱዳን በእግር ኳሳዊ መመዘኛዎች ስትለካ በብዙ ርቀት ወደ ኋላ የተገኘች ሀገር ናት አሁን ላይ። ኢትዮጵያ ለሞሮኮው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከዴሞክራቲክ ኮንጎ፣ ከጊኒ እና ታንዛኒያ ጋር በምድብ ስምንት ተደልድላ ነበር። ሀገራችን በምድቡ ካደረገቻቸው ስድስት ጨዋታዎች በአራቱ በመሸነፍ፣ በአንዱ አቻ በመውጣት እና ከምድቧ ቀድማ ማለፏን ያረጋገጠችውን ዴሞክራቲክ ኮንጎን በማሸነፍ በአራት ነጥብ የምድቡን የመጨረሻ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን አንድ ጊዜ መውሰድ ብትችልም በሂደት በመድረኩ እያስመዘገበች ያለችው ውጤት ግን የቁልቁለት ጉዞ ኾኗል። በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በብሔራዊ ቡድኑ እየተመዘገበ ያለው ውጤት አንገት የሚያስደፋ ኾኗል፡፡ በአንጻሩ ጎረቤት ሱዳን በጦርነት ምክንያት ክለቦቿም ኾኑ ብሔራዊ ቡድኗ በሊቢያ ሜዳዎች ላይ እየተጫወቱ ለሞሮኮው የአፍሪካ ዋንጫ ማለፏና አልሃሊም በአፍሪካ የክለቦች ሻምፒዮና ወደ መጨረሻው የምድብ ድልድል መግባት መቻሉ ከወዲህ ለውጤት ማጣት የሚነሱ ምክኒያቶች ላይ ጥያቄ ያስነሳል።

ዋሊያዎቹ የካፍን መመዘኛ የሚያሟላ ስታዲየም ስለሌላቸው በስደት ስድስት ጨዋታዎችን ለማድረግ ቢገደዱም፣ የስታዲየም አለመኖር ብቻውን የሽንፈት ምክንያት እንደማይኾን ከሱዳን ብሔራዊ ቡድን ውጤት መረዳት ይቻላል፡፡ ይባስ ብሎ ብሔራዊ ቡድኑ በቻን የማጣሪያ ጨዋታ በሱዳን በደርሶ መልስ ተሸንፎ ለውድድሩ ማለፍ አለመቻሉ ከምክኒያቶች በላይ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ ማሳያ ነው።

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህሩ ደምስ ጋሹ (ዶ.ር) ˝የኢትዮጵያ እግር ኳስ ሕመም በሁሉም ብሔራዊ ቡድናችን ላይ ነው˝ ብለዋል፡፡ በፊፋ የደረጃ ሠንጠረዥ 148ኛ ላይ መገኘታችን፣ በአፍሪካ ከመጨረሻዎቹ 10 ሀገራት ተርታ መገኘታችን፣ በሴቶችም ኾነ በወንዶች የብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች እና የክለቦች ጨዋታዎች ከውጤት መራቃችን፣ በሁሉም የዕድሜ እርከኖች ተሸናፊ መኾናችን እና ሌሎችም ምክንያቶች ሲደማመሩ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ሕመም ሁለንተናዊ ነው ማለት ይቻላልም” ብለዋል ዶክተር ደምስ፡፡

ብሔራዊ ቡድኑ የሚዋዥቅ ውጤት የሚያስመዘግበው በዋነኛነት ወጥነት ያለው ሥልጠና ስለሌለ ነው የሚሉት ዶክተር ደምስ፣ በተጨዋቾቹ መሸነፍ እና ማሸነፍ ውስጥ በጉልህ የሚታየው የአሠልጣኞቹ ደካማ ሥራዎች ናቸው ሲሉም የእግር ኳሱን ሕመም መንስኤ ጠቁመዋል፡፡የኢትዮጵያ እግር ኳስ ሕመም ከአሠልጣኞቹ ባሻገር እግር ኳሱን ከሚመሩት አካላት የሚመነጭ ነው፤ እግር ኳሱ የሚመራው በሙያው ሰዎች አይደለም ያሉት ዶክተር ደምስ ሙያተኞች መሪዎችን ለመደገፍ ሲያስቡ እንኳን በእንጀራቸው እንደገቡባቸው የሚቆጥሩ የእግር ኳሱ አሥተዳዳሪዎች በርካታ ናቸው ብለዋል፡፡ እግር ኳስም ኾነ ሌሎች ስፖርቶች በሙያተኞች እንጂ በፖለቲከኞች ሲመሩ የሚገኘው ውጤት መጥፎ እንደሚኾንም ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ አካዳሚዎች ባይኖሩም፣ ባሉት ውስጥም ቢሆን በክለቦች አከባቢ የሚታየው እግር ኳስን በሙያና በሙያተኛ የመምራት ችግር በአካዳሚዎች ውስጥም ይታያል ያሉት ዶክተሩ፣ በውጭ ሀገራት ባሉ የታዳጊዎች ማሠልጠኛ ወይም አካዳሚዎች ውስጥ ለታዳጊዎቹ የሚሰጣቸው ሥልጠና ሁለንተናዊ ነው፡፡

የአካል ብቃት፣ የአመጋገብ፣ የክህሎት እና ሌሎች ሥልጠናዎች እንደሚሰጡም ባለሙያው አንስተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሜዳው ውጭ መጫወቱ፣ የደጋፊዎችን ድጋፍ ማጣቱ እና ከሀገር ሀገር እየዞረ መጫወቱ መጠነኛ ክፍተቶችን ሊፈጥር ይችላል ያሉት ባለ ሙያው፣ ኢትዮጵያ ለሞሮኮ የአፍሪካ ዋንጫ ላለመቅረቧ ብቸኛው ምክንያቷ ግን ስታዲየም ማጣቷ ሊሆን አይችልም ብለዋል፡፡

˝እግር ኳስ በስሜት ሳይሆን በስሌት የሚደረግ ጨዋታ ነው˝ ያሉት ዶክተር ደምስ የብሔራዊ ቡድናችን አሠልጣኞች የማንንም ብሔራዊ ቡድን አንፈራም ከሚል ዛቻቸው ይልቅ ማንንም የማይፈራ ጠንካራ ቡድን መገንባት አለባቸው ሲሉ መክረዋል፡፡ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ዴሞክራቲክ ኮንጎን ያሸነፈችው ከሜዳዋ ውጭ መኾኑን ያስታወሱት ዶክተሩ፣ በሜዳችን ለብዙ ጊዜ መሸነፋችንንም አንስተው በሜዳ መጫወት የእግር ኳሳችን ማከሚያ ዘዴ እንደማይኾንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ በእጅጉ ታሟል፡፡ መድኃኒቱ የሚገኘው ደግሞ ከመንግሥት፣ ከባለ ሃብቶች፣ ከስፖርት ባለሙያዎች፣ ከተጨዋቾች፣ ከአሠልጣኞች፣ ከደጋፊዎች፣ ከስፖርቱ ቤተሰቦች እና ከሌሎችም ነው ሲሉ ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡ በአንድ ወቅት አይቮሪኮስት የውስጥ ሰላሟን ስታጣ እነ ዲዲዬር ድሮግባ እና ሌሎችም ተጨዋቾች ለሀገራቸው ሰላም መኸቀን እግር ኳስን በመሣሪያነት ተጠቅመዋል፡፡

ሱዳን በእርስ በርስ ግጭት አሳሯን እያየች ባለችበት በዚኽ ክፉ ወቅት ብሔራዊ ቡድኗ እና ክለቧ አልሃሊ በትላልቅ መድረኮች ውድድራቸውን ያደርጋሉ፤ በእነዚህ ጨዋታዎች የሱዳን ሕዝብ የሀገር ውስጥ ችግሩን ለአፍታም ቢኾን ዘንግቶ ለሀገራቸው ውጤታማነት በአንድነት ይቆማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ስፖርት የተኳረፈን ያስታርቃል፤ ቂምን አስረስቶ እርስ በእርስ ያስተቃቅፋል። ይሄ በተለያየ ጊዜ በኮትዲቯር፣ ደቡብ አፍሪካ እና መሰል ሀገራት ታይቷልና።

ዘጋቢ:- እሱባለው ይርጋ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here