ሥድስተኛው የፋሲል ከነማ የሩጫ ጥር አራት ቀን ይካሄል፡፡

0
209

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የፋሲል ከነማ ስፓርት ክለብን ለማጠናከር ጥር አራት ለሚካሄደው የአምስት ኪሎ ሜትር ሩጫ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ማኅበር አስታውቋል፡፡ በጥምቀት ለምትሞሸረው ጎንደር ከተማ ሌላኛው ድምቀት ይኾናል የፋሲል ከነማ ሩጫ። ላለፋት አምስት ዓመታት ሲካሄድ ቆይቷል።

በዚህ ዓመትም ጥር አራት ቀን ለስድስተኛ ጊዜ ሩጫው ይካሄዳል፡፡ በሩጫ ውድድሩ ከግማሽ ምዕተ ዓመት የተሻገረ ዕድሜ ላለው ስፓርት ክለብ የማጠናከሪያ ገቢ ይሰበሰብበታል ተብሎ ይጠበቃል። የሩጫ ውድድሩን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ የደጋፊዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ብርሃኑ በውድድሩ 10 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ገቢ ለመሠብሠብ መታቀዱን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እየተሳተፈ የሚገኘው ፋሲል ከነማ በገቢ እራሱን ለማጠናከር የተለያዩ ሥራዎች ሢሠሩ መቆየታቸውንም ተናግረዋል፡፡ ከ15 ሺህ እስከ 20 ሺህ የሚደርሱ ደጋፊዎች በውድድሩ ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አንስተዋል፡፡ አምስት ኪሎ ሜትር በሚሸፍነው የጎዳና ላይ ውድድር የክለቡን የደጋፊዎች አብሮነትን እና ቤተሰባዊ ግንኙነት የሚያጠናክር መኾኑም ተነግሯል።

የፋሲል ከነማን የገቢ አቅም ለማጠናከር በሚደረገው ውድድር የመሮጫ መለያ መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል፡፡ የክለቡ ደጋፊዎች እና የስፖርት አፍቃሪያን በተለያዩ አማራጮች የቀረበውንን ማሊያ በመግዛት ክለቡን እንዲያበረታቱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳንኤል ወርቄ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here