የእነ ሀይሌ እና ደራርቱ የሙያ አባት!

0
175

ባሕር ዳር: ኅዳር 23 /2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኦሎምፒክ እና ዓለም ሻምፒዮና ሀገራቸውን ከፍ ያደረጉ፤ ክብረወሰን ሰባሪ ድንቅ አትሌቶችን አፍርተው ኢትዮጵያውያንን በድል ያስተቃቀፉ እና በደስታ እንባ ያራጩ የሀገር ባለውለታ ናቸው ወልደመስቀል ኮስትሬ(ዶ.ር)። ሰውየው ዓመታትን በተሻገረው የአትሌቲክስ አሠልጣኝነታቸው ደራርቱ፣ ኃይሌ፣ ቀነኒሳ፣ መሰረት እና ጥሩነሽን የመሳሰሉ ለማሸነፍ ብቻ የተፈጠሩ አትሌቶችን አፍርተዋል። በኦሎምፒክ ታሪክ በ13 ወርቅ፣ 5 ብር እና 10 ነሐስ በድምሩ በ28 ሜዳልያ ሀገራቸውን ያደመቁ የጀግኖች የሙያ አባት ናቸው።

ቀጥተኛ እና ላመኑበት ሟች፣ በሀገር ፍቅር የሚታወሱ ምርጥ ኢትዮጵያዊ ናቸው ይሏቸዋል በቅርብ የሚያውቋቸው። በ1939 ዓ.ም ወደዚህ ዓለም መምጣታቸውን የሪፖርተር የቆየ እትም መረጃ ያሳያል። ቦታው በያኔው አጠራር ተጉለት እና ቡልጋ አውረጃ ሳሲት እንግድ ዋሻ ነው። በልጅነታቸው ከትምህርት ጎን ለጎን ሩጫን ይወዱ እንደነበር በሕይወት በነበሩበት ጊዜ ሲገልጹ ተሰምተዋል። በ400፣ 800 እና 1ሺህ 500 ሜትሮች ጎበዝ ሯጭም ነበሩ። አበበ ቢቂላ ከሮም በኋላ በደመቀበት የቶኪዮ ኦሎምፒክ ዶክተር ወልደመስቀል ሀገራቸውን በመካከለኛ ርቀት ወክለው የመወዳደር ዕድል ነበራቸው። ነገር ግን የውጭ የትምህርት ዕድል በማግኘታቸው ለትምህር ቅድሚያ ሰጥተው ወደ ሀንጋሪ አቀኑ።

ከትምህርት መልስ በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ሥራ ጀምረው ወዲያው ወደ አሠልጣኝነት ገብተዋል። በ1972 የሙኒክ ኦሎምፒክ የወቅቱ ዋና አሠልጣኝ እሸቱ ቱራ ረዳት በመኾን አሠልጣኝነትን ጀምረዋል። ከዚያም እንደገና ወደ ሀንጋሪ ተጉዘው የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። ከሀንጋሪ ተመልሰው በስፖርት ኮሚሽን ለጥቂት ጊዜያት ሠርተዋል። በእነዚህ ጊዜያት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን እና ለቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ የአካል ብቃት አሠልጣኝ ኾነው አገልግለዋል።

የዶክተር ወልደመሰቀል የረዥም ርቀት ሩጫ መሐንዲስነት የጀመረው ደራርቱ ታሪክ በሠራችበት የባርሴሎና ኦሎምፒክ ነው። ከአሠልጣኝ እሸቱ ቱራ የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝነትን ተረክበው በባርሴሎ እና በደራርቱ የ10 ሺህ ሜትር ገድል ራሳቸውን አስተዋውቀዋል። የወቅቱ የደራርቱ ድል ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይኾን ለአፍሪካውያንም አዲስ ነገር ነበር።

በዚህ መንገድ ደራርቱን ለዓለም ያስተዋወቁት ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ እስከ 2008ቱ የቤጅንግ ኦሎምፒክ ድረስ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ነበሩ። በእነዚህ ጊዜያት ደራርቱ፣ ኃይሌ፣ ቀነኒሳ፣ መሰረት እና ጥሩነሽን የመሳሰሉ የሀገር ኩራት የኾኑ አትሌቶችን አፍርተዋል።
በኦሎምፒክ ብቻ በ13 ወርቅ፣ 5 ብር እና 10 ነሐስ በድምሩ በ28 ሜዳሊያ የሀገር ግርማ ሞገስ ከፍ እንዲል የሠሩ ሰው ናቸው። በተለይ ረዥም ርቀት እና ኢትዮጵያ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ እንዲባል የእኝሁ ቆፍጣና ሠው ሥራ የሚመሠገን ነው። ለዚህም ይመስላል “ብዙዎች የረዥም ርቀቱ መሀንዲስ” ብለው የሚጠሯቸው።

ከኦሎምፒክ በተጨማሪ በዓለም ሻምፒዮናም “አረንጓዴው ጎርፍ” በረዥም ርቀት ዓለምን ሲያስከነዳ ቆፍጣናው ተጉለቴ ከፊት ነበሩ። አትሌቶች ሥራቸውን እንዲያከብሩ፣ ሀገራቸውን እንዲያስቀድሙ እና በቡድን ሥራ እንዲያምኑ የማይጣስ ቀይ መስመር አስቀምጠው ማነጻቸው ለአትሌቶችም ኾነ ለራሳቸው ስኬታማነት እና ለሀገር ክብር ከፍ ማለት ቁልፉ ነገር መኾኑን በሕይወት በነበሩ ጊዜ ደጋግመው ተናግረዋል።

እጅግ ሀገራቸውን የሚወዱ፣ ላመኑበት ወደ ኋላ የማይሉ ቆራጥ እና ቆፍጣና ይሏቸዋል በቅርብ የሚያውቋቸው። የቀድሞው የኢቲቪ የስፖርት ጋዜጠኛ ታደለ አሰፋ ከዓመታት በፊት የእንቁውን ሰው ህልፈት ተክትሎ “ዶክተር ወልደ መስቀልን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ መነጠል አይቻልም፤ ለሀገር ክብር ብዙ የደከሙ፣ ቀጥተኛ እና ለዕውነት የሚሞቱ፣ ለሀገር እንጂ ለራሳቸው ሳይሉ የኖሩ” ብሏቸዋል።

“ደራርቱ፣ ኃይሌ፣ ቀነኒሳ፣ መሰረት እና ጥሩነሽን የመሰሉ ክብረወሰን ሰባሪ ሯጮችን በኢትዮጵያዊ ቆራጥነት ያፈሩ፤ ለብዙ አሠልጣኞችም የሙያ መንገድ መሪ” ሲሉ የገለጿቸው ደግሞ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኀላፊነት የሚታወቁት ቢልልኝ መቆያ ናቸው።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ በትልልቅ የሩጫ ውድድሮች የሚመጥናት ውጤት እያገኘች አይደለም። ይህ እንዳይመጣ ዶክተሩ ሞት ሳይቀድማቸው ምክር ለግሰው ነበር። “አሠልጣኞች አትሌቶችን ቆፍጠን ብላችሁ ምሩ፣ እነቀነኒሳ ኃይሌን፤ እነጥሩነሽ ደራርቱን የተኩበትን መንገድ ተከትላችሁ ወጣቶች ላይ ሥሩ፤ ሀገርን አስቀድሙ” ብለው ነበር።

ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ የዓለም አትሌቲክስ ማኅበር የዓመቱ ምርጥ አሠልጣኝ ብሎ የሸለማቸው፣ አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት በሚያማልል ገንዘብ የአሠልጥኑልን ጥያቄ የቀረበላቸው ግን ቅድሚያ ለሀገሬ ብለው ሀገርን ያስቀደሙ ነበሩ።

ይሄ የሀገር ፍቅራቸው ከድል በኋላ ሀገራቸውን በማኩራታቸው በደስታ የሚያነቡ፣ ወድቀው በመነሳት ከህመማቸው ጋር ታግለው ሰንደቅን ከፍ የሚያደርጉ እና በውድድር መሐል የቡድን አጋርን ፍለጋ ወደ ኋላ የሚያማትሩ ድንቅ ሯጮችን እንዲያፈሩ አድርጓቸዋል። በእነዚያ ዘመናት መላ ኢትዮጵያውያን ከእነ ቀነኒሳ እና መሰረት ጋር አብረው ሩጠዋል፣ በደስታ ተቃቅፈዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here