የሲቲ ደጋፊዎች በቡድናቸው ላይ ተቃውሞ አሰምተዋል።

0
168

ባሕር ዳር: ኅዳር 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ)

ማንቸስተር ሲቲ በአምስተኛው ዙር የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ በኢትሃድ ስታዲየም ከኔዘርላንዱ ፌይኑርድ ጋር አቻ ተለያይቷል። ከውጤት በኋላ ጋርዲዮላ ቡድናቸውን “ደካማ” ብለው ገልጸውታል። በጨዋታው እስከ 74ኛው ደቂቃ 3 ለ 0 ሲመሩ የቆዩት ሲቲዎች ውጤቱን ማስጠበቅ ተስኗቸው ከ74ኛው ደቂቃ ጀምሮ ፌይኑርድ ሦስት ተከታታይ ግቦችን አስቆጥሮ አቻ ለመለያየት ተገደዋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የክለቡ ደጋፊዎችም ተቃውሞ አሰምተዋል። ይሄም በቅርብ ዓመታት በውጤታማነት ጉዞ በሚገኘው ሲቲ ቤት የተለመደ አይደለም። ሲቲ ከ1963 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሁሉም ውድድሮች በስድስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሁለት እና ከዚያ በላይ ግቦችን አስተናግዷል።

የፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮኖቹ የሞራል ብቃትን በማጎልበት የዋንጫ ተቀናቃኛቸው ሊቨርፑልን ለመግጠም ይዘጋጃሉ ቢባልም በአቻ ውጤት መጨረሳቸው በቀጣዩ ጨዋታ ላይ የተፎካካሪነታቸው ነገር ጥያቄን እንዲያጭር አድርጓል ሲል ቢቢሲ በስፖርት ገጹ አስነብቧል፡፡ በኢትሃድ ስታዲየም ተገኝቶ ጨዋታውን የተከታተለው የቀድሞ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አምበል አለን ሸረር “ደካሞች ናቸው” ሲል የጋርዲዮላን አስተያዬት አጠናክሮታል።

ይህ ብቻ ሳይኾን አሠልጣኙ ቡድናቸውን መምራት ተስኗቸው እንዴት ማሸነፍ እንደሚቻል የረሱ ይመስላሉ ነው ያለው። ማንቸስተር ሲቲ በሻምፒዮንስ ሊጉ ከአምስት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው በሁለት ጨዋታዎች ብቻ ነው። በሁለቱ አቻ ወጥቶ በአንዱ በመሸነፍ በስምንት ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በቀጣይ ሲቲ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ከሊቨርፑል ጋር ይጫወታል። በሁለቱ ቡድኖች መካከል የስምንት ነጥብ አለ። በአንፊልዱ ጨዋታ ሲቲ ከተሸነፈ የዋንጫ ተፎካካሪነቱ አስቸጋሪ ይኾናል።

አሁን የጋርዲዮላው ቡድን እያሳየ ካለው ደካማ አቋም አንጻር አንፊልድ ላይ ነጥብ ማግኘቱም በብዙ ያጠራጥራል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here