“ህልሙን የተከተለ ሰው ብላችሁ አስታውሱኝ”።

0
261

ባሕር ዳር: ኅዳር 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለማችን ላይ ስም እና ምግባራቸው ለብዙ ወጣቶች አርዓያ ከሚኾኑ ሰዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የሜዳ ቴኒስ ስፖርት ሲነሳ ስማቸው በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ጥቂት ሰዎች ውስጥም አንደኛው ነው፡፡ ከአራት ዓመቱ ጀምሮ የጨበጠውን የቴኒስ ራኬት በቃኸኝ ብሎ ሲሰናበት ከሁለቱም በየአቅጣጫው አስተያየቶች እየተነሱ ነው፡፡ ከ20 ዓመት በላይ በፍቅር የተጫወተውን የሜዳ ቴኒስ ጨዋታ እና ሜዳዎቹን የተሰናበተውም በእንባዎቹ ታጅቦ ነው፡፡

ለዓመታት የእሱን ጨዋታ በመመልከት ድጋፋቸውን እና ፍቅራቸውን የለገሱትን ተመልካቾችም የተሰናበታቸው በከፍተኛ ሀዘን ውስጥ ኾኖ ነው፡፡ ሙሉ ስሙ ራፋኤል ናዳል ፓሬራ ይባላል፡፡ ናዳል ማክሰኞ ምሽት በተካሄደው የዴቪስ ካፕ ውድድር ሀገሩን ስፔንን ወክሎ ከተጫወተ በኋላ ራሱን ከፕሮፊሽናል የሜዳ ቴኒስ ውድድሮች አግልሏል፡፡

በ21ኛው ክፍለ ዘመን በስፖርት ስማቸውን በትልቁ ከገነቡት ጥቂት ሰዎች ውስጥ አንዱ የኾነው ራፋኤል ናዳል ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተደጋጋሚ ጊዜ ያጋጠሙት ጉዳቶች ከሚወደው የሜዳ ቴኒስ ራሱን እንዲያቅብ ምክንያት እንደኾነ የቢቢሲ፣ ስካይ ስፖርት እና ዩሮ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ራፋኤል ናዳል 22 የግራንድ ስላም ውድድሮችን በማሸነፍ ብቸኛው የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ነው፡፡ ስምንት ውድድሮችን በተከታታይ በማሸነፍም የሚስተካከለው ተጨዋች የለም፡፡ ሁለት የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያዎችን ለሀገሩ ስፔን እና ለራሱ በማስገኘትም የሜዳ ቴኒስ ተጨዋችነት ክብሩን በወርቅ ሜዳሊያዎች ጭምር ያጀበ ነው ራፋኤል ናዳል፡፡

በአደገኛ የግራ እጅ ልጎቹ (ሰርብ) የሚታወቀው ራፋ ወደ ሜዳ ቴኒስ ስፖርት የገባው ሁለት በስፖርት ውስጥ ያለፉ አጎቶቹን በማየት ነው፡፡ ሚጊዌል አንሄል ናዳል የተባሉት አንደኛው የራፋኤል ናዳል አጎት በ2002 ለስፔን ብሔራዊ ቡድን በግብ ጠባቂነት የተጫወቱ ሲኾን፣ ሌላኛው አጎቱ ቶሚ ናዳል ደግሞ በቴኒስ አሠልጣኝነታቸው የሚታወቁ ናቸው፡፡

ራፋኤል ናዳል በሕጻንነቱ ጽሑፎችን የሚጽፈው በቀኝ እጁ ሲኾን በአራት ዓመቱ ላይ ቴኒስ ይጫወት የነበረው ደግሞ በግራ እጁ እንደነበረ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ናዳል 12 ዓመት ሲሞላው አጎቱ ቶሚ በግራ እጁ ቢጫወት ይበልጥ ውጤታማ እንደሚኾን መክረውታል፡፡

እ.ኤ.አ በ2001 ፕሮፌሽናል የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች የኾነው ናዳል በ2002 በዌምበልደን የሜዳ ቴኒስ ውድድር በወጣቶች ዘርፍ ተጫውቶ እስከ ግማሽ ፍጻሜ መድረስ ችሏል፡፡ ይሄው ውጤቱም የናዳል የወደፊት ቀናት ብሩህ እንደኾኑ ያመላከተ ነበር፡፡

በ2005 ታዳጊ ኾኖ በ11 ትልልቅ ውድድሮች ላይ አሸናፊ የኾነ የመጀመሪያው የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ተብሎ ”በአሶሴሽን ኦፍ ፕሮፌሽናል” ስም ዝርዝር ውስጥ ስሙን ማካተት ችሏል፡፡

በ2007 በብዙ ስኬቶች የታጀበው ናዳል በጀርመን ሀምቡርግ በተካሄደው የሜዳ ቴኒስ ውድድር በስዊዘርላንዳዊው ሮጀር ፌዴረር ተሸንፏል፡፡

በ2008 በዌምበልደን ታሪክ 4 ሰዓት ከ48 ደቂቃ በፈጀው የፌዴረር እና የናዳል ፍልሚያ በናዳል አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሲሆን በዌምበልደን የሜዳ ቴኒስ ውድድሮች ታሪክ ረጅም ሰዓት የፈጀው ውድድር ኾኖም ተመዝግቧል፡፡

ራፋኤል ናዳል ኖቫክ ጆኮቪችን፣ ሮጀር ፌዴረርን እና ሌሎችንም የዘመኑን ምርጥ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋቾች በእርስ በርስ ፉክክሮች በማሸነፍ ባለ ክብረ ወሰን ተጨዋችም ጭምር ነው፡፡

ራፋኤል ናዳል ከሜዳ ውጪም ”ራፋ ናዳል ፋውንዴሽን”ን አቋቁሞ ትምህርታቸውን መከታተል ያልቻሉ ልጆችን በማገዝ ሰብዓዊነቱን አሳይቷል፡፡

ናዳል የስፔኑ ሪያል ማድሪድ ቀንደኛ ደጋፊ እንደኾነ ይነገራል፤ ከአብዛኞቹ የሪያል ማድሪድ ተጨዋቾች ጋርም ጓደኛ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ የማድሪድ ደጋፊዎች የእሱን ውድድሮች እንደሚከታተሉት ሁሉ እሱም የነሱን ጨዋታ በቤርናባው እና በሌሎች ስታዲየሞች እየተገኘ ይከታተላል፡፡

ራፋኤል ናዳል በማኅበራዊ የትሥሥር ገጾች ለአብነትም በኢንስታግራም ከ21 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ተከታይ እና በትዊተርም ከ15 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ተከታዮችን ያፈራ ተጽዕኖ ፈጣሪ የስፖርት ሰው ነው፡፡

በ38 ዓመቱ ከፕሮፌሽናል የሜዳ ቴኒስ ራሱን ያገለለው ራፋኤል ናዳል እንደ መልካም ሰው እና ህልሙን እንደተከተለ ሰው ኾኖ መታወስ እንደሚፈልግ በስንብቱ ወቅት ተናግሯል፡፡

በእርግጥም ራፋ በሁሉም የስፖርት ዓይነቶች ለሚሳተፉ ወጣቶች ምርጥ አርዓያ ኾኖ ከሜዳ ቴኒስ ስፖርት እንደተሰናበተ የሚስማሙት ብዙዎች ናቸው፡፡

ዘጋቢ፡- እሱባለው ይርጋ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here