ለአካባቢው ወጣቶች ተስፋ የሰጠው የዱርቤቴ ስታድየም ውጥን።

0
219

ባሕር ዳር: ኅዳር 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ጎጃም ዞን የዱርቤቴ ከተማ አሥተዳደር በ2017 በጀት ዓመት ከሚሠራቸው ዋና ዋና ሥራዎች ውስጥ የስፖርት ማዘውተሪያ ስታዲየሙን ግንባታ አንዱ መኾኑ ተገልጿል። የስታድየሙ የመሠረት ድንጋዩንም የዞኑ ከፍተኛ መሪዎች እና የከተማው ኅብረተሰብ በጋራ አኑረዋል።

የዱርቤቴ ነዋሪ እና የመንግሥት ሠራተኛ አማረ ብርሃኑ የስፖርት ማዘውተሪያ ሁለገብ ስታዲየም ለመገንባት በመታቀዱ ደስተኛ መኾኑን ገልጿል። የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጥ ብቻ ሳይኾን ወደ ተግባር መገባት እንዳለበት አሳስቧል። ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም እንዲገነባም ኅብረተሰቡ በጉልበት እና በገንዘብ እንዲያግዝ እናስተባብራለን ብሏል።

ወጣት ብርሃኑ ያዜ ደግሞ የእግር ኳስ ዳኛ ነው። በዱርቤቴ ከተማ ሁለገብ ስታዲየም ለመገንባት መሠረት መቀመጡ ትልቅ ነገረነው አለን። ወጣቶች ወደ አልባሌ ቦታ ከመሄድ ያድናቸዋል፤ ከሕጻናት እስከ አዋቂዎች ጤናቸውን ይጠብቁበታል፤ ኅብረተሰቡም ስፖርት ወዳድ ስለኾነ ብዙ ፋይዳ እንደሚኖረው ነው የገለጸው።

ኅብረተሰቡ ለግንባታው በገንዘብ፣ በጉልበቱ እና በዕውቀቱ እንዲያግዝ እንደሚያስተባብሩም ነው ቃል የገቡት። ኅብረተሰቡም በባለቤትነት ስሜት መጎትጎት እና መከታተል እንዳለበትም ገልጸዋል። በዱርቤቴ ከተማ አሥተዳደር የወጣቶች እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፈንታሁን አሰፋ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለት ስታዲየም ወጣቱ አልባሌ ቦታ እንዳይውል ታስቦ በ40 ሺህ 593 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፍ ካርታ እና ፕላን የተዘጋጀለት ሁለገብ የስፖርት ስታዲየም መኾኑን ጠቅሰዋል።

ሥራውን በ2017 የበጀት ዓመት ለማስጀመርም ከከተማ አሥተዳደሩ አንድ ሚሊዮን ብር ተመድቧል ብለዋል። ቁሳቁስም መገዛት ተጀምሯል፤ ስታዲየሙ ሲጠናቀቅ በዙሪያው የሚገኘውን የአቸፈር እና ሜጫ ወረዳዎችንም እንደሚያገለግል ተናግረዋል። ከወጣቱ እና ሌላው ማኅበረሰብ ጋር በመወያየትም በፍጥነት ይጠናቀቃል ነው ያሉት ኀላፊው።

“ስፖርትን ጨምሮ ወጣቱ የሚጠቀምበትን እና ከአልባሌ ቦታ የሚርቅበትን ኹኔታ ለማመቻቸት መሪዎች በትኩረት እየሠራን ነው” ብለዋል ኀላፊው።

አሁን ላይ የተመደበው የግንባታ በጀት ከመንግሥት ሲኾን ከስፖርት ምክር ቤቱ እና ከማኅበረሰቡም የበጀት ድጋፍ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here