ባሕር ዳር: ጥር 3/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሐ ግብር ዛሬ ቀን 9 ሰዓት ላይ ወልቂጤ ከተማ ከፋሲል ከነማ እንዲኹም ምሽት 12 ሰዓት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወላይታ ድቻ ይጫወታሉ፡፡
በፕምየር ሊጉ ወልቂጤ ከተማ ከዘጠኝ ጨዋታዎች በሁለቱ አሸንፎ፣ በሁለቱ አቻ ወጥቶ እና በአምስቱ ተሸንፎ በዘጠኝ የግብ ዕዳ በስምንት ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ቡድኑ ከመቻል ጋር ባካሄደው የስምንተኛ ሳምንት ጨዋታ በዋናነት መከላከል ላይ ያተኮረ አቀራረብ ይዞ መቅረቡ ይታወሳል፡፡ ይሁንና በመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ ከሌላው ጊዜ በተሻለ ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ጥረት አድርጓል።
አሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት በመጨረሻዎቹ ሳምንታት በተከተሉት ተቀያያሪ አሰላለፍ ምክንያት በዛሬው ጨዋታ የሚጠቀሙት የአሰላለፍ ስልት ለመገመት ያዳግታል፡፡ ከተጋጣሚው የአማካይ እና የአጥቂ ጥንካሬ አንጻር ኳስን ከመቆጣጠር ይልቅ ግብ ላይ ያተኮረ አቀራረብን ይዞ ይገባል ተብሎ ይገመታል።
በወልቂጤ ከተማ በኩል ተስፋዬ መላኩ እና ሳምሶን ጥላሁን በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም። ወንድማገኝ ማዕረግ ግን ከጉዳት ተመልሷል። ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ድሬዳዋ ከተማን ሦስት ለባዶ ያሸነፉት አፄዎቹ ከዘጠኝ ጨዋታዎች አራቱን አሸንፈዋል፡፡ በሦስቱ ደግሞ አቻ ወጥተዋል፡፡ በሁለቱ ተሸንፈው እና በስድስት የግብ ክፍያ በአስራ አምስት ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።አፄዎቹ በጉልህ ይታይባቸው የነበረውን የግብ ማስቆጠር ችግር እየፈቱ ይገኛሉ፡፡ ድሬዳዋ ከተማን ያሸነፉበትን ጨዋታ ለአብነት ማንሳት በቂ ይኾናል፡፡
በፋሲል ከነማ በኩል አማኑኤል ገብረሚካኤል፣ ኢዮብ ማቲያስ፣ ፍቃዱ ዓለሙ እና ሸምሰዲን መሐመድ በጉዳት ምክንያት በዛሬው ጨዋታ አይሰለፉም ተብሏል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ስድስት ጊዜ ተገናኝተዋል፡፡ ፋሲል በሦስት ጨዋታዎች ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ያለ ጎል አቻ ተለያይተዋል፡፡ በአንድ ጨዋታ ደግሞ ወልቂጤ አሸንፏል።
ጨዋታውን ሔኖክ አበበ በመሐል ዳኝነት ይመሩታል፤ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት እና ሰለሞን ተስፋዬ በረዳት ዳኝነት ተመድበዋል፡፡ ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ አራተኛ ዳኛ ኾነው ተሰይመዋል፡፡
ምሽት 12 ሰዓት ላይ ደግሞ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወላይታ ድቻ ይጫወታሉ፡፡ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ካምፓኒ (EPLSC ) መረጃ መሰረት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ ዘጠኝ ጨዋታዎችን በማድረግ በሰባቱ አሸንፎ፣ በሁለቱ አቻ ወጥቶ በ11 ንጹህ የግብ ክፍያ 23 ነጥብ በመሰብሰብ በአንደኛነት ተቀምጧል፡፡ በመኾኑም ቡድኑ በጥሩ አቋም ላይ ይገኛል፡፡
አሠልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ በሁሉም ረገድ የተሟላና ሚዛኑን የጠበቀ ቡድን ገንብተዋል ማለት ይቻላል፡፡ በዛሬው ጨዋታ በዘጠኝ ሳምንታት አስር ግብ ላስተናገደው የወላይታ ድቻ የተከላካይ ክፍል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጥቂዎች ትልቅ ፈተና ይኾኑበታል ተብሎ ይገመታል፡፡
በንግድ ባንክ በኩል ፍቃዱ ደነቀ በጉዳት አይሰለፍም፡፡ ቅጣት ላይ የነበሩት ሱሌማን ሀሚድ እና ሲሞን ፒተር ደግሞ ቅጣታቸውን ጨርሰው ለጨዋታ ዝግጁ ናቸው። በዘጠነኛው ሳምንት ላይ ወልቂጤ ከተማን ሁለት ለአንድ በማሸነፍ ከሽንፈት ቶሎ ያገገሙት ወላይታ ድቻዎች በአስራ አራት ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
የጦና ንቦች በሊጉ ጠንካራ የአማካይ ክፍል ካላቸው ቡድኖች ይመደባሉ፡፡ በዛሬው ጨዋታም ጠንካራ የአማካይ ክፍል ካለው ቡድን ጋር እንደመጫዎታቸው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ የሚደረገው ፍልሚያ የጨዋታውን ውጤት ይወስነዋል ተብሎ ይገመታል።
የጦና ንቦች የተከላካይ ክፍል በጥሩ ወቅታዊ የግብ ማስቆጠር ብቃት ላይ ያለውን የንግድ ባንክ ተከላካይ ክፍል እንቅስቃሴ የመግታት ትልቅ ኃላፊነት ይጠብቀዋል።
በሊጉ የመጀመሪያ ሳምንታት ላይ የግብ ዕድሎች የመጠቀም ችግር የተስተዋለበት የቡድኑ የአጥቂ ጥምረትም በጊዜ ሂደት ጥሩ መሻሻል ቢያሳይም ዛሬ ግን የንግድ ባንክን የተከላካይ ክፍል መፈተን የሚያስችል አቅም ማጎልበት ይኖርበታል።
በወላይታ ድቻ በኩል አጥቂው ባዬ ገዛኸኝ እና ተከላካዩ መልካሙ ቦጋለ ከዛሬው የጨዋታ ስብስብ ውጭ ናቸው። ሶከር ኢትዮጵያ እንደዘገበው ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ስምንት ጊዜ ተገናኝተዋል፡፡ ሁለት ሁለት ጊዜ አሸንፈዋል፡፡ በአራት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ወላይታ ድቻ ዘጠኝ ግብ አስቆጥሯል፡፡ ንግድ ባንክ በአንጻሩ ሰባት ግብ በወላይታ ድቻ መረብ ላይ አሳርፏል፡፡
ይህንን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው (ዶ.ር) ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ እና ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ አሸብር ታፈሠ ረዳት ዳኛ በመኾን ይመሩታል፡፡ ዓባይነህ ሙላት ደግሞ አራተኛ ዳኛ ኾነው ተመድበዋል።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!