ባሕር ዳር: ጥቅምት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአውሮፓ ዋንጫ ሻምፒዮንስ ሊግ አራተኛ ጨዋታዎች ትናንት ምሽት ተጀምረዋል። በትናንት ምሽት ጨዋታዎች ያልተጠበቁ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ የቻምፒዮንስ ሊግ ባለ ታሪኩ ማድሪድ በሜዳውና በደጋፊው ፊት በኤሲሚላን ተሸንፏል። ከኤልክላሲኮ የሜዳ ላይ ሽንፈት አጎበር ሳይላቀቅ ሌላኛውን ጨዋታ ያደረገው ማድሪድ ድጋሜ እጁን ሰጥቷል፡፡
ወደ ፖርቹጋል የተጓዘው የፔፕ ጋርዲዮላው ማንቸስተር ሲቲም በስፖርቲንግ ሊዝበን ያልታሰበ ሽንፈት ገጥሟል። ማድሪድና ማንቸስተር ሲቲ ትናንት ምሽት በተጋጣሚዎቻቸው በሰፊ ልዩነት መሸነፋቸው ብቻ ሳይኾን በተደጋጋሚ ጨዋታዎች መሸነፋቸው ምን ነካቸው እያስባለ ነው፡፡ ማድሪድ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን ሲሸነፍ፣ ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎችን ተሸንፏል፡፡
የማድሪድ እና የሲቲን ድክመት ያጋለጠው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዛሬም ቀጥሎ ዘጠኝ ጨዋታዎች በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች ይደረጋሉ። ኢንተር ሚላን ከአርሰናል፣ ፒኤስጅ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ምሽት ከሚካሄዱ ጨዋታዎች መካከል ትኩረት ያገኙ ናቸው። አርሰናል ወቅታዊ ብቃቱ የሚመሰገን አይደለም። የመጨረሻ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታውንም ተሸንፏል። የአምበሉ ኦዶጋርድ መመለስና ወደ ጣሊያን መጓዝ ግን ለአርሰናል ትልቁ ዜና ነው፡፡
በሻምፒዮንስ ሊጉ ደግሞ ሁለቱ ክለቦች እስካሁን የሰበሰቡት ነጥብ ተመሳሳይ ነው። ሁለቱን አሸንፈው በአንዱ አቻ በመለያየት እኩል ሰባት ነጥብ ይዘው ነው ዛሬ በኢንተሩ ሜዳ ጆሲፔ ሜዛ የሚገናኙት። አርሰናል ከጣሊያን ሦስት ነጥቦችን ይዞ ወደ እንግሊዝ ይመለሳል ወይስ የፕሪሚዬር ሊጉ ድክመቱ ተከትሎት እጅ ነስቶ ይመለሳል የሚለው ይጠበቃል፡፡
ሌላኛው ተጠባቂ ጨዋታ ፈረንሳይ ላይ ፒኤስጅን ከአትሌቲኮ ማድሪድ ጋር የሚያገናኘው ነው። ሁለቱ ክለቦች በሻምፒዮንስ ሊጉ በሦስቱ ጨዋታዎች ያደረጉት እንቅስቃሴ ደካማ ነው። ፒኤስጅ አራት አትሌቲኮ ደግሞ ሦስት ነጥቦችን ብቻ ይዘዋል። በሌሎች ጨዋታዎች ክለብ ብራግ ከአስቶን ቪላ፣ ሻካታር ዶኔስክ ከያንግ ቦይስ፣ ባየር ሙኒክ ከቤኔፊካ፣ ፌይኖርድ ከአርቢ ሳልዝበርግ ይጫወታሉ።
ሬድ ስታር ከባርሴሎና፣ ስፓራታ ፕራግ ከ ስቴድ ብረስቶስ፣ ስቱትጋርት ከአታላንታ በተመሳሳይ የዛሬ መርሐ ግብሮች ናቸው። ትናንት ታላላቆቹን አንገት ያስደፈው የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ዛሬስ ምን ያሳይ ይኾን? የሚለው ትኩረት ስቧል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!