አዲሱ ፈርጉሰን እየመጣ ይሆንን?

0
227

ባሕር ዳር: ጥቅምት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሜዳ የማይጠፉትን ነገር ግን እንደ ድሮው ለክብሩ የማይወድቁትን ታላቅ ሰው ካጣ ዓመታት አልፈዋል፡፡ በክብር መቀመጫቸው ተቀምጠው በዓለም እግር ኳስ ያነገሡት ክለብ ሲሰባበር በሃዘን ሲመለከቱት ኖረዋል፡፡ ባለዙፋን ሲነሳ ባለዙፋን መተካት ልማድ ኾኖ ሳለ የእርሳቸውን ግርማ የሚያስቀጥል ወራሽ ሳይገኝ ዓመታት ነጉደዋል፡፡ ለወትሮው እንግዳ ቡድኖችን እግራቸውን የሚያርደው ኦልድትራፎርድ ዛሬ ላይ ግርማውን ተነጥቋል፡፡ ታላላቆቹም ታናናሶቹም በድፍረት ገብተው በድፍረት የሚወጡበት ኾኗዋል፡፡

ከታላቁ የእግር ኳስ ሰው ሰር አሌክስ ፈርጉሰን መልቀቅ በኋላ አሠልጣኞች ተቀያየሩ፣ አንዳቸውም ግን ለፈርጉሰን ወንበር የተገቡና የሚመጥኑ አልነበሩም፡፡ ተስፋ እየተጣለባቸው የሚመጡት ሁሉ የመጨረሻ እጣቸው ኦልድትራፎርድን በደብዳቤ እየለቀቁ መሰናበት ኾነ፡፡ አሠልጣኞችን በመቅጠር እና በማሰናበት የተጠመደው ማንቸስተር ዩናይትድ ኔዘርላንዳዊውን ኤሪክ ቴን ሃግን አሰናብቶ ፖርቹጋላዊውን ወጣት አሠልጣኝ ሩበን አሞሪምን ሾሟል፡፡ ፖርቹጋላውያን ኦልድትራፎርድን ያውቁታል፡፡ ታሪክም ሰርተውበታል፡፡ የዓለም ኮኮቡ ክርስቲያኖ ሮናልዶ የገናናነት ታሪኩን የጀመረው በኦልድትራፎርድ ነው፡፡ ቄንጠኛው ናኒም በኦልድትራፎርድ የማይረሳ ፖርቹጋላዊው ነው፡፡ የአኹኑ የማንቸስተር አምበል ብርኖ ፈርናንዴስም ከወደ ፖርቹጋል የመጣ ታታሪ ነው፡፡

ልዩው ሰው እየተባሉ የሚሞካሹት ጄሴ ሞሪኒሆም በኦልድትራፎርድ የመሰናበት እጣ ከደረሳቸው አሠልጣኞች መካከል ቢኾኑም የኢሮፒያ ሊግ ዋንጫን ያመጡ ፖርቹጋላዊ ናቸው፡፡ የአሁኑ የመስመር ተከላካዩ ዲያጎ ዳሎትን ጨምሮ ሌሎች ፖርቹጋላውያንም የማንቸስተር ዪናይትድን ቤት ያውቁታል፡፡ አሁን ደግሞ ሌላኛው ፖርቹጋላዊ ወጣት አሠልጣኝ ኦልድትራፎርድ ደርሷል፡፡ በፖርቹጋል እግር ኳስ አዲስ አቢዮተኛ የተባለው የ39 ዓመቱ አሠልጣኝ በስፖርቲንግ ሊዝበን እግር ኳስ ክለብ ተወዳጁ ሰው ነው፡፡

ስፖርቲንግ ሊዝበንን ከዓመታት የዋንጫ ረሃብ በኋላ ወደ ክብር የመለሰው አሞሪም የመጪው ዘመን ተስፈኛ አሠልጣኝ እየተባለ ነው፡፡ የታላላቅ የአውሮፓ እግር ኳስ ክለቦችን ጥያቄ ውድቅ አድርጎ ለማንቸስተር ዩናይትድ ይኹንታውን የሰጠው ሩበን አሞሪም አዲሱ ፈርጉሰን እየተባለ ነው፡፡ ሊሰናበተው ጥቂት ቀናት የቀሩትን ስፖርቲንግ ሊዝበንን ይዞ በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር የተገናኘው ሩበን አሞሪም በፔፕ ጋርዲዮላ ላይ ድል ተቀዳጅቷል፡፡

በማንቸስተር ከተማ ከማንቸስተር ሲቲ ብርቱ ፉክክር የሚገጥመው አሞሪም ማንቸስተር ዩናይትድን ከመረከቡ አስቀድሞ የወደፊት ተቀናቃኙን ድል መትቶ መጣሁላችሁ ማለቱ “አዲሱ ፈርሰጉሰን እየመጣ ነው” እያስባለው ነው፡፡ ስካይ ስፖርት በዘገባው የቀጣዩ የማንቸስተር ዩናይትድ አሠልጣኝ ሩብን አሞሪም ማንቸስተር ሲቲን ያሸነፈበት ጨዋታ ለቀጣዩ ጉዞው ትምህርት የሚሰጥ ነው ብሏል፡፡ ሩብን አሞሪም በማንቸስተር ሲቲ ላይ የተቀዳጀው ድል የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች አዲሱ ፈርጉሰን እየመጣ እንደኾነ ሊያስቡ ይችላሉ ነው ያለው፡፡

ነገር ግን ከአኹኑ እንዲህ አይነት ንጽጽር መሥራት ከባድ ሊኾን ይችላል ብሏል፡፡ ሩበን አሞሪም ማንቸስተር ሲቲን ድል ካደረገ በኋላ በማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች ዘንድ የተፈጠረው ደስታ ታላቅ እንደኾነ ተመላክቷል፡፡ የትናንት ምሽቱ ድል የተለየ እንደነበር የተናገረው ወጣቱ አሠልጣኝ ሩበን አሞሪም ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲሄድ የተለየ ዓለም እና የተለየ ጫና እንደሚጠብቀው ነው የተናገረው፡፡

አሞሪም ሲቲን ያሸነፈበትና ከመመራት ተነስቶ ጨዋታውን የቀየረበት መንገድ የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች ተስፋቸው ላቅ እንዲል አድርጎታል፡፡ ፖርቹጋላዊው ወጣት አሠልጣኝ በትናንቱ ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ የሰጠው ምላሽ የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊዎችን ተስፋ ከፍ እንዲል ካደረጉ ምክንያቶች አንደኛው ነው ብሏል ስካይ ስፖርት፡፡ ቡድኑ ከመመራት ተነስቶ አራት ግቦችን በማስቆጠር ድል ነስቷልና፡፡

ዘ ጋርዲያን ሩበን አሞሪም ማንቸስተር ሲቲን ድል ከመቱ በኋላ አዲሱ ፈርጉሰን የሚል ስም እንደተለጠፈበት አመላክቷል፡፡ አዲስ ስለተሰጠው ስያሜም ሩበን አሞሪም ደጋፊዎች አዲሱ ፈርጉሰን እንደኾንኩ ሊያስቡ ይችላሉ፣ ነገር ግን አስቸጋሪ መኾኑን ተናገሯል፡፡

ወደ ኦልድትራፎርድ ከመምጣቱ ዋዜማ የምንጊዜም ተቀናቃኛቸውን ለረታላቸው አሞሪም አዲሱ ፈርጉሰን ብለው የዩናይትድ ደጋፊዎች ሙገሳ ሰጥተዋል። ታዲያ ይሄ ተስፋና ጉጉት በኦልድትራፎርድ እውን ይኾንን? የሚለው አኹንም ጊዜ የሚፈታው ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥ የወጣቱን አሠልጣኝ ተስፋና የእግር ኳስ ክህሎት ያዩ ሰዎች ማንቸስተር ዩናይትድን ወደቀደመ ክብሩ የሚመልሰው ትክክለኛው ሰው ነው ይላሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የቀድሞ ተጫዋቾች እና የሚዲያዎች ትችት የሚበዛበት ቤት ለአዲሱ አሠልጣኝ ከባድ ፈተና እንደሚኾን ይጠበቃል።

ወጣቱ አሠልጣኝ ከቀናት በኋላ ሀገሩ ፖርቹጋልን ተሰናብቶ፣ በሊዝበን የሠራውን ድንቅ ታሪክ እያስታወሰ ወደ አዲሱ ቤቱ ወደ እንግሊዝ ማንቸስተር ያመራል፡፡ በማንቸስተር ከተማ በታላቁ ክለብ ፊት አዲስ ታሪክ ይጽፍ ይኾን? ወይንስ እንደሌሎቹ አሠልጣኞች በውጤት ቀውስ ምክንያት የመሰናበቻ ደብዳቤ ይደርሰዋል የሚለው ጊዜ ይፈተዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here