ባሕር ዳር: ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በድሬ ዳዋ ከተማ እየተካሄደ ባለው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በዛሬው ሰባተኛ መርሐ ግብር ቀን 10 ሰዓት ፋሲል ከነማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ። ፋሲል ከነማ እስካሁን ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው ቅዱስ ጊዮርጊስን ብቻ ነው። በአራት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቶ በአንዱ ደግሞ ተረትቷል።
ቡድኑ ሰባት ነጥብ በመያዝም 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በመኾኑም ዛሬ ከአምስት ድል አልባ ጉዞው ለመውጣት ብርቱ ፉክክር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። በጨዋታ ረገድ አጼዎቹ በአምስት ጨዋታዎች ከድል ጋር ቢራራቁም በኳስ ቁጥጥር ረገድ ግን የተሻሉ ነበሩ። ነገር ግን ቡድኑ ኳስ እና መረብን የማገናኘት ድክመቱን ዛሬ አርሞ መቅረብ ይኖርበታል።
ለፋሲል ከነማ ከሰባት ወራቶች ጉዳት የተመለሰው አማኑኤል ገብረሚካኤል ልምምድ ቢጀምርም ለዛሬው ጨዋታ ግን አይደርስም ተብሏል። የፋሲል ተፎካካሪ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሦስተኛ ድሉን ለማሳካት ነው ዛሬ የሚጫወተው። እንደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ድረ ገጽ ቡድኑ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች የተሸነፈው በአንድ ጨዋታ ብቻ ሲኾን በሁለቱ ጨዋታዎች ደግሞ አሸንፏል። በዘጠኝ ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
የቡድኑ የመከላከል አቅም ጠንካራ ነው። በመኾኑም ዛሬ ለፋሲል ጨዋታ ከባድ ፈተና መኾኑ አይቀርም። ኢትዮ ኤሌክትሪክ በጉዳትም ኾነ በቅጣት የሚያጣው ተጫዋች የለም። ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ሰባት ጊዜ ተገናኝተዋል። ፋሲል ከነማ አራት ጊዜ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ደግሞ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፉ በአንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።
ምሽት 1:00 ደግሞ ኢትዮጵያ ቡና ከስሑል ሽረ ይጫወታሉ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!