ባሕር ዳር: ጥቅምት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ከብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች መልስ ቅዳሜ እና እሑድ ይመለሳሉ። የስምንተኛ ሳምንት መርሐ ግብሮችን የሚያከናውነው የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግም ነገ ቶትንሃም ከዌስትሃም በሚያደርጉት የደርቢ ጨዋታ ይጀምራል። በስምንተኛ ሳምንት ከሚካሄዱ ጨዋታዎች መካከል በአንፊልድ ሊቨርፑል ቼልሲን የሚገጥምበት ጨዋታ ይበልጥ ይጠበቃል። በሊቨርፑል ቤት ለጊዜውም ቢኾን የክሎፕ መልቀቅ ቁጭት አልፈጠረም። ምክኒያቱም ተተኪያቸው ስሎት መንገዳቸው የቀና ኾኗልና ነው፡፡
ቀዮቹ ሊጉን በመምራት ላይ ናቸው። በሰባት ጨዋታ ስድስቱን አሸንፈው፣ በአንዱ ተሸንፈዋል። በተለይ በሳላህ የሚመራው የሊቨርፑል የአጥቂ ክፍል በርካታ ግቦችን እያስቆጠረ ይገኛል። ቼልሲ በአዲሱ አሠልጣኝ ማሬስካ የተሻለ መነሳሳት እያሳየ ነው። ከመሪው እና የሳምንቱ ተጋጣሚው ሊቨርፑል በአራት ነጥብ አንሶ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ክለቡ ግቦችን በማስቆጠር እና በመከላከል በኩል በማሬስካ ሥር ከኾነ በኋላ ለውጦችን አሳይቷል። እንግሊዛዊ ኮል ፓልመር ደግሞ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ነው።
እሑድ 12:30 የሚካሄደው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች በጥሩ ብቃት ላይ ኹነው የሚያደርጉት በመኾኑ ትኩረት ስቧል። ጨዋታው በአሚኮ አዲስ ኤፍ ኤም 103 ነጥብ 5 ቀጥታ ይተላለፋል። ሌሎች የሳምንቱ ጨዋታዎችም ሲቀጥሉ ቅዳሜ ሰባት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። 8:30 ቶትንሃም ከዌስትሃም ይገናኛሉ። በተመሳሳይ 11 ሰዓት ላይ ደግሞ በብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ምክኒያት ከተነሳባቸው እሳት በመጠኑ እፎይ ብለው በሰነበቱት ቴንሃግ የሚመራው ዩናይትድ ከብሬንት ፎርድ፣ ፉልሃም ከአስቶን ቪላ፣ ኒውካስትል ከብራይተን፣ ኢፕስዊች ከኤቨርተን እና ሳውዝ አምፕተን ከሌስተር ይጫወታሉ።
ምሽት 1:30 ላይ ደግሞ በፕሪምየር ሊጉ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርሰናል ከሜዳው ውጭ በርንማውዝን ይገጥማል። እሑድ ከተጠባቂው የሊቨርፑል እና ቼልሲ ጨዋታ በፊት 10 ሰዓት ላይ በሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ሲቲ ከሜዳው ውጭ ከዎልቭስ ጋር ይፋለማል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!