ባሕር ዳር: ጥቅምት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ የወንዶች እግር ኳስ ቡድን ለ2025 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ አራት ጨዋታዎችን አድርጎ አንድ ነጥብ ብቻ አስመዝግቧል፡፡ ዋሊያዎቹ በአራት ጨዋታዎች ኳስ እና መረብን ማገናኘት የቻሉት አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡
ዋሊያዎቹ በምድብ ስምንት ከታንዛኒያ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ጊኒ ጋር ነው የተደለደሉት። ከታንዛኒያ ጋር ያለ ግብ አቻ ውጤት፣ በዴሞክራቲክ ኮንጎ የ2 ለ 0 ሽንፈት፣ በጊኒ የ4 ለ 1 ሽንፈት እንዲኹም ከጊኒ ጋር ባደረጉት የመልስ ጨዋታ ደግሞ 3 ለ 0 ተሸንፈዋል፡፡ “ዋሊያው ቀንድ አልባ ነው” ለማለት ያስደፈረንም በአራት ጨዋታዎች በተቃራኒዎቹ መረብ ላይ ያሳረፈው ግብ ብዛት አንድ ብቻ በመኾኑ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ግብ አግቢ እየኾኑ የሚያጠናቅቁት የውጭ ሀገር ተጨዋቾች ናቸው፤ ለአብነትም በ2015 የውድድር ዘመን ኮከብ ግብ አግቢ ኾኖ ያጠናቀቀው የቶጎው እስማኤል ኦሮ አጎሮ ነው፡፡ በ2016ትም ኮከብ ግብ አስቆጣሪ መኾን የቻለውም ኤርትራዊው አሊ ሱሌይማን ነበር።
ኢትዮጵያውያኑ የፊት መስመር ተሰላፊዎች ጎልን ከመረብ ጋር ለማገናኘት የመቸገራቸውን ያህል የተከላካይ እና ግብ ጠባቂ ቦታው ደግሞ በአንድ ተጫዋች ብቻ በሁለት ጨዋታ አምስት ግብ የሚያዘንብበት ነው። የቡድኑ የመሃል ሜዳ ክፍልም ቢኾን ቡድኑ ጎል እዲያስቆጥርም ይሁን እንዳይቆጠርበት የነበረው ድርሻ በጥሩ የሚነሳ አለመኾኑን የተጠቀሱት ቁጥሮች እማኝ ናቸው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ከ20 ዓመት በታች የወንዶች ቡድንም በምሥራቅ አፍሪካ የማጣሪያ ጨዋታዎች ከሦስት ጨዋታዎች፣ በሦስቱም ተሸንፎ፣ ከዘጠኝ ቡድኖች በስምንተኛ ደረጃ ጨዋታውን ጨርሶ ዋናው ብሔራዊ ቡድን ተተኪዎችን እያፈራ አለመኾኑን አሳይቶን አልፏል፡፡ ይሄ ደግሞ የብሔራዊ ቡድኑ ህመም ዛሬ ብቻ ሳይኾን ለነገም እንዳይሻገር ያስፈራል።
የአፍሪካ ዋንጫ መስራቹ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በውድድሩ ለመሳተፍ ግን እየተቸገረ ነው። ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ መሠረተው የአፍሪካ ዋንጫ ቢመለስም ለሌላ ውድድር ደግሞ ስምንት ዓመታትን መጠበቅ ግድ ሆኖበታል፡፡ ከስምንት ዓመታት በኋላ ካሜሮን ባዘጋጀችው የ33ኛው አህጉራዊ ውድድር ላይ የተሳተፉት ዋሊያዎቹ ከተሳትፎ ባልዘለለ መልኩ በመጀመሪያው ዙር ተሰናባች እና የምድባቸውንም ግርጌ ይዘው ያጠናቀቁ ኾነዋል፡፡
በ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ መሳተፍ ያልቻለችው ሀገር ሞሮኮ በምታስተናግደው በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይም የመሳተፍ እድሏ ተራራ እንደ መግፋት የከበደ ኾኗል። በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የማይታደሙት የዋሊያዎቹ ሥብሥብ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት ካለመጫወቱ በተጨማሪ ምን ዓይነት ክፍተቶች እንደነበሩበት የቀድሞው የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው እና በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር ደምስ ጋሹ (ዶ.ር) አስተያየታቸውን አጋርተውናል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ34ኛው እና 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ላለመሳተፉ ዋነኛው ችግሩ ጥሩ ተጨዋቾችን ማጣቱ ብቻ ሳይኾን ጥሩ አሠልጣኞችን ማጣቱ ጭምር ነው ይላሉ ዶክተር ደምስ። የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኞች የዕለት ጨዋታን የማንበብ ብቃት የሌላቸው፣ የተጋጣሚ ቡድንን ጥንካሬ እና ድክመት የማይለዩ፣ የተለያዩ የአጨዋወት ዕቅዶችን ነድፈው ለዚያ አጨዋወት የሚኾኗቸውን ተጨዋቾች መለየት ያልቻሉ ናቸው። በእነዚሁ የአሠልጣኞች የብቃት ውስንነትም ብሔራዊ ቡድኑ ዋጋ ከፍሏል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡
“የሀገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞችን የሚመለምልበት መንገድ ስህተት መኾኑን ብሔራዊ ቡድኑ ከሚያስመዘግባቸው ደካማ ውጤቶች መረዳት ይቻላል። በአሠልጣኞቹ መካከል የሚታየው እንደ ቡድን ያለመሥራት ችግር በተጨዋቾቹም ዘንድ በግልጽ የሚታይ ችግር ነው” ብለውናል፡፡
እንደ እንግሊዝ ባሉ ታላላቅ ክለቦች ውስጥ ውጤት ያላመጡ አሠልጣኞች ቶሎ ቶሎ የሚቀያየሩት ለክለቦቹ ውጤት ማጣት ቀዳሚዎቹ ተጠያቂዎች አሠልጣኞቹ ስለሆኑ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን የሚያሠለጥኑ አሠልጣኞች ከተጨዋቾች አመጋገብ አንስቶ፣ ልምምዶችን እና ቋሚ ተሰላፊነትን በግላቸው (በሞኖፖል) ስለሚሠሩ አሠልጣኞቹ እንደ ቡድን የሚያስመዘግቡትን ውጤት እያየን አይደለም ሲሉም ዶክተር ደምስ አሠራሮችን ተችተዋል፡፡
“በኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም ደረጃ የሚታዩት የክለቦች ጨዋታዎች ጠንካራ ፉክክር የሚታይባቸው አይደሉም።” ለዚህ ደግሞ የተጨዋቾችም ኾነ የአሠልጣኞች ቅጥር ችሎታ ተኮር ባለመሆኑ ሲሉም አክለዋል የስፖርት ሳይንስ መምህሩ፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ ለእግር ኳስ የሚወጣው ወጪ ከፍተኛ ቢሆንም ወጪውን የሚመጥኑ ተጫዋቾችን መፍጠር ያለመቻል የሙያ ክፍተትን በግልጽ እየታየ ነው ብለዋል።
የሀገሪቱ እግር ኳስ እንዲያድግ ከተፈለገ በወንዶች፣ በሴቶች፣ በወጣቶች እና በታዳጊዎች ላይ ጠንካራ ሥራዎች መሠራት ይኖርባቸዋል፡፡ ከጊዜያዊ ውጤት ፍለጋ አባዜ ወጥቶ በፕሮጀክት የሠለጠኑ ስፖርተኞችን በማፍራት የሀገሪቱን የእግር ኳስ መሠረት በጠንካራ አለት ላይ መገንባት ያስፈልጋል በማለትም ዶክተር ደምስ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡ ስፖርቱን በሙያተኞች መምራትም የመፍትሄው አካል እንዲኾን አሣሥበዋል፡፡
የእግር ኳስ ጨዋታ ማንም ሰው እንደፈለገው የሚጫወትበት ሳይኾን ለሙያው ተሰጥኦ ያላቸው ሕጻናት ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ ክህሎታቸውን የሚያሳድጉበት ሙያ ነው፤ ያሉት ደግሞ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ናቸው፡፡ ዕድሜ ከገፋ በኋላ እግር ኳስን መጀመር ስህተት ቢኾንም በኛ ሀገር ግን የሚዘወተረው አካሄድ ይሄኛው እንደኾነ ኢንስትራክተሩ ገልጸዋል፡፡
እግር ኳስን መጫወት ያለባቸው በዘርፉ መክሊት ያላቸው ልጆች እንጂ ፍላጎቱ ስለኖረን ወይም ገንዘብ ስለሚያስገኝ መኾን የለበትም ያሉት ኢንስትራክተር ሰውነት፣ እግር ኳስን መጫወት ብቻ ሳይኾን ተጨዋቾችን ለማሠልጠን እና የእግር ኳስ አሥተዳደሩንም ለመምራት የሙያው ሰው መኾንን ይጠይቃል ብለዋል፡፡ በእኛ ሀገር ግን ይሄ ሁሉ ያልተለመደ በመኾኑ የእግር ኳሳችን ውጤት የምናየውን ኾኗል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውጤታማ እንዲኾን ከተፈለገ ሳይንሳዊ አሠራሮችን መከተል ያስፈልጋል ብለዋል። የቀድሞው የብሔራዊ ቡድኑ ውጤታማው አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው ተሰጥኦ ያላቸው ሕጻናት በባለሙያ ሠልጥነው ውጤታማ እንዲኾኑ ማድረግ ይቻላል ብለው እንደሚያምኑ አንስተዋል፡፡ የውጭ ክለቦች እና ብሔራዊ ቡድኖች በአካዳሚ ፍሬዎቻቸው ያገኙትን ጥሩ ውጤትም እንደ አብነት ጠቅሰዋል፡፡
ለእግር ኳሳችን ትንሳኤ በእግር ኳስ ላይ ብዙ መዋዕለ ነዋይ ማፍሰስ ብቻ ሳይኾን የማዘውተሪያ ሥፍራዎችን ማብዛት፣ ሳይንሳዊ ሥልጠናዎችን መስጠት፣ ውድድሮችን ማዘጋጀት እና ሌሎችንም ተግባራት በአግባቡ መፈጸም ይገባልም ብለዋል፡፡ ይሄን ማድረግ ከተቻለ በረጅም ጊዜም ቢኾን ሀገራችን ወደ ውጤታማነት ትመለሳለች የሚል ሃሳባቸውንም ሰንዝረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- እሱባለው ይርጋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!