ዝነኛው የቴንስ ተጫዋች ራፋኤል ናዳል ከቴንስ ጨዋታ ሊገለል ነው፡፡

0
252

ባሕር ዳር: መስከረም 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ)ዝነኛው የቴንስ ተጫዋች ራፋኤል ናዳል ከቴንስ ጨዋታ ራሱን ሊያገልል መኾኑን ተናግሯል፡፡ ዓለም ካየቻቸው ድንቅ የሜዳ ቴንስ ተጫዋቾች መካከል አንደኛው እንደኾነ ይነገራል፡፡ ለዓመታት በዘለቀ የሜዳ ቴንስ ተጋድሎ በርካታ ክብሮችን አሳክቷል፡፡
በእግር ኳስ በበርካታ ከዋክብት የምትታወቀው እና የምትጠራው ስፔን በሜዳ ቴንስ ደግሞ በራፋኤል ናዳል ትጠራለች፡፡ ዝነኛ ነው፡፡ ብዙዎች ያደንቁታል፡፡

ገና በለጋ ዕድሜው ከቴንስ ጋር ተዋውቆ በዓለም ላይ ስሙ ናኝቷል፡፡ ስሙንም በሜዳ ቴንስ ታሪክ ደመቅ አድርጎ አጽፏል፡፡ ብዙዎች በእርሱ ብቃት እና ብርታት ተደንቀውበታል፡፡ አርዓያቸውም አድርገውታል፡፡ እርሱ ያሳካቸውን ስኬቶች ለማሳካት የሚታትሩ በርካታ ወጣቶች እንዲፈጠሩ ምክንያት ኾኗል ናዳል፡፡

የክሌይ ንጉሥ እያሉ ይጠሩታል፡፡ በሜዳ ቴንስ ደምቋልና፡፡ ታላላቅ የእግር ኳስ ሰዎችን ጨምሮ ዓለም አቀፍ አድናቂዎች ያሉት ራፋኤል ናዳል በ2024 የሜዳ ቴንስ እንደሚያቆም ተናግሯል፡፡ የ22 ጊዜ የግራንድ ስላም ሻፒዮናው ናዳል ጉዳት በሜዳ ቴንስ ተጫዋችነቱ እንዳይቀጥል እንዳደረገው ተነግሯል፡፡ ናዳል በኅዳር ወር ከሚካሄደው የዴቭስ ካፕ የፍጻሜ ፍልሚያ በኋላ መጫወት እንደሚያቆም አስታውቋል ብሏል ሮይተርስ በዘገባው፡፡

በ23 ዓመታት በነበረው የሜዳ ቴንስ ተጫዋችነት ዘመኑ 14 የፈረንሳይ ኦፕን ክብረ ወሰኖችን አሸንፏል፡፡ ጉዳት ሕይዎቱን እንደፈተነው ያመላከተው የሮይተርስ ዘገባ ጡረታ እንደሚወጣ አስቀድሞ ተናግሮ እንደበር አስታውሷል፡፡ የ38 ዓመቱ ናዳል በኅዳር ወር በስፔን ማላጋ በሚካሄደው የዴቭስ ካፕ የፍጻሜ ጨዋታ በኋላ በቃኝ ይላል ነው የተባለው፡፡

ናዳል በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባስተላለፈው በተንቀሳቃሽ ምስል የታገዘ መልዕክት በጉዳት ያሳለፈባቸው ዓመታት በጣም አስቸጋሪዎች እንደነበሩ ተናገሯል፡፡ በተለይም የመጨረሻዎቹ ሁለት ዓመታት ከባዶች እንደነበሩ ነው ያስታወሰው። የመጨረሻው ውድድር ሀገሩን የሚወክልበት በመኾኑ መደሰቱንም ተናግሯል፡፡

ኤቲፒ ቱር የተባለ ድሕረ ገጽ ራፋኤል ናዳል በ2024 የውድድር ዘመን መጨረሻ የሜዳ ቴንስ ጨዋታ በቃኝ እንደሚል ማስታወቁን ዘግቧል፡፡ የ38 ዓመቱ ስፔናዊ ናዳል እ.አ.አ ከኅዳር 19 እስከ 24 በማላጋ የሚካሄደው የዴቪስ ዋንጫ የመጨረሻ ጨዋታው እንደሚኾን አስታውቋል ነው ያለው፡፡
ናዳል የተጫዋችነት ዘመኑን እንደሚያበቃ በተናገረበት መልዕክቱ ይህን ውሳኔ ለመወሰን የተወሰነ ጊዜ የፈጀብኝ ከባድ ውሳኔ እንደኾነ ግልጽ ነው ብሏል፡፡

ነገር ግን በዚህ ሕይዎት ውስጥ ሁሉም ነገር መጀመሪያ እና መጨረሻ አለው፡፡ እናም ለረጅም ጊዜ የቆየ ሥራን ለማቆም ትክክለኛው ጊዜ ነው ብዬ አስባለሁ ነው ያለው። ካሰብኩት በላይ በጣም ስኬታማ ጊዜ ነበር ማለቱን ኤቲፒ ቱር ዘግቧል፡፡ ለ209 ሳምንታት ወይም ለአራት ዓመታት የሜዳ ቴንስ የዓለም ቁጥር አንድ ኾኖ የቆየው ናዳል በተጫዋችነት ዘመኑ ታላላቅ ክብሮችን አሳክቷል ነው የተባለው፡፡

ናዳል በሜዳ ቴንስ ታላቅ ስም ካላቸው ኖቫክ ጆኮቪች እና ሮጀር ፌደረር ጋር ሲታወስ እንደሚኖርም ተመላክቷል፡፡ ሦስቱ ባለታሪክ ተጫዋቾች በሜዳ ቴንስ ታሪክ ታላቅ ስም ገንብተዋልና፡፡ ቢቢሲም የሜዳ ቴንስ ባለታሪኩ ናዳል ከዴቪስ ዋንጫ በኋላ ራሱን ከቴንስ ተጫዋችነት እንደሚያገል ዘግቧል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት በጉዳት ምክንያት እምብዛም ያልተጫወተው ናዳል በ2024 መጨረሻ በቃኝ እንደሚል ተናግሯል ብሏል ቢቢሲ፡፡

“የክሌይ ንጉስ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ናዳል ካደረጋቸው 116 ዋና ዋና ግጥሚያዎች 112ቱን አሸንፏል፤ 14 ጊዜ ደግሞ በፈረንሳይ ኦፕን አሸናፊ የኾነባቸው ናቸው፡፡ የፈረንሳይ ኦፕንን 14 ጊዜ ያሸነፈው ናዳል ይሄም ክብረ ወሰን ነው ብሏል ቢቢሲ፡፡ የቀደሞው የዓለም ቁጥር አንዱ ናዳል አሁን ላይ እየደረሰበት ካለው ጉዳት አንጻር እንደቀድሞው ሁሉ እየተጫወተ አይደለም፡፡

ለወትሮው በሜዳው እንዳሻው የሚወረወረው ናዳል ጉዳቱ የቀድሞ ብቃቱን አውጥቶ እንዳይጫወት አድርጎታል፡፡ ገና በልጅነቱ ከሜዳ ቴንስ ጋር የተዋወቀው ናዳል በ15 ዓመቱ ወደ ፕሮፌሽናልነት ተሸጋግሯል፡፡ እ.አ.አ በ2004 ስፔን በዴቪስ ዋንጫ አሜሪካን ስትረታ ናዳል የዓለም ቁጥር ሁለት የኾነውን አንዲ ሮዲክን በማሸነፍ ታሪክ ሠርቷል ይላል ቢቢሲ፡፡

ይሄም ታሪክ ለናዳል ከማይረሱ አስደሳች ጊዜያት መካከል እንደኾነ ተናግሯል፡፡ ናዳል የማይረሳ ታሪክ በጻፈበት በዴቪስ ዋንጫም የመጨረሻውን ጨዋታ አድርጎ ይሰናበታል፡፡ ናዳል በዘመኑ 22 ጊዜ የግራንድ ስላምን፣ 14 ጊዜ የፈረንሳይ ኦፕንን፣ ሁለት አወስትራሊያን ኦፕን፣ ሁለት ጊዜ ዌንብልደንን፣ አራት ጊዜ ዩኤስ ኦፕንን፣ ሁለት የኦሎምፒክ ወርቆችን፣ አራት ጊዜ የዴቪስ ካፕ፣ 92 የኤቲፒ ቱር ክብሮችን ማሳካቱን እና ለ209 ሳምንታት ደግሞ የዓለም ቁጥር አንድ ኾኖ መቆየቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ታዲይ ይህ የሜዳ ቴንስ ጀግና ነው በ2024 መጨረሻ መጫወት አቆማለሁ ያለው፡፡

የናዳል የስኬት ዘመናት ሮጁር ፌዴረር፣ ኖቫክ ጀኮቪች እና ለተወሰነ ጊዜ ደግሞ አንዲ ሜሪይ ስፖርቱን በተቆጣጠሩበት ዘመን እንደነበር ስካይ ስፖርት አስነብቧል፡፡ ጎል ዶት ኮም በዘገባው ራፋኤል ናዳል በ21ኛው ክፍለ ዘመን በስፖርቱ ዓለም ታላላቅ ስም ካላቸው ስፖርተኞች መካከል አንደኛው እንደኾነ አመላክቷል፡፡ የሪያል ማድሪድ እግር ኳስ ቡድን የልብ ደጋፊ እንደኾነም ዘግቧል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here