ባሕር ዳር: መስከረም 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የቀድሞው የሼፊልድ ዩናይትድ ተጫዋች ጆርጅ ባልዶክ በ31 ዓመቱ ሕይዎቱ ማለፉ ተነግሯል፡፡ እንግሊዝ ውስጥ የተወለደው ግሪካዊው ጆርጅ ባልዶክ በግሪክ ዋና ከተማ አቴንስ ውስጥ በሚገኘው ቤቱ መዋኛ ገንዳ ውስጥ ሕይዎቱ አልፎ ተገኝቷል፡፡
ሮይተርስ ጆርጅ ባልዶክ በመዋኛ ገንዳ ውስጥ ሞቶ ተገኝቷል ብሏል፡፡ ሮይተርስ የፖሊስ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ግሪካዊ ተከላካይ በመዋኛ ገንዳው ሞቶ ተገኝቷል ነው ያለው፡፡ ተጫዋቹ መሞቱ እንጅ የሞተበት ምክንያት እስካሁን አለመታወቁን ነው ሮይተርስ የዘገበው፡፡
ለሀገሩ ግሪክ ብሔራዊ ቡድን 12 ጨዋታዎችን የተጫወተው ጆርጅ ባልዶክ ሼፊልድ ዩናይትድን ከለቀቀ በኋላ የግሪኩን ፓናቲናይኮስ ተቀላቅሏል፡፡
የተከላካይ መስመሩ ተጫዋች ከሼፊልድ ዩናይትድ ጋር የተለያየው ክለቡ ከእግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ከወረደ በኋላ መኾኑንም ሮይተርስ በዘገባው አመላክቷል፡፡ ተጫዋቹ በእግር ኳስ ዘመኑ ለኤም ኬ ዶንስ እና ኦክስፎርድ ዩናይትድ መጫወቱ ነው የተነገረው፡፡ ሰባት ዓመታትን በሼፊልድ ዩናይትድ የተጫወተው ጆርጅ ባልዶክ ሕይዎቱ ማለፉን ተከትሎ የቀድሞ ክለቡ ሼፊልድ ዩናይትድን ጨምሮ ሌሎች የእንግሊዝ ክለቦች ሀዘናቸውን እየገለጹ መኾኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ባልዶክ ለአዲሱ ክለቡ ፓናቲናይኮስ አራት ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡ ክለቡ ፓናቲናይኮስ ከ ኦሎምፒያኮስ ጋር ባደረጉት የሳምንቱ የእረፍት ቀን ጨዋታዎች ላይ ተጫውቶ እንደነበር ነው የተነገረው፡፡ ተጫዋቹ ለሀገሩ ብሔራዊ ቡድን እንዳልተጠራ ተነግሯል፡፡ ሀገሩ ግሪክ በኔሽኒስ ሊግ ዛሬ ምሽት ከእግሊዝ ጋር በዌንብሌይ ትጫወታለች፡፡ ተጫዋቹ ግን ሀገሩ ከመጫዋቷ አስቀድሞ ሕይዎቱ አልፏል፡፡
ቢቢሲም በዘገባው ተጫዋቹ ረቡዕ መሞቱ ከመሰማቱ አስቀድሞ እሑድ በጨዋታ ተሳትፎ እንደነበር አስታውሷል፡፡ ዛሬ ከእንግሊዝ ጋር የሚጫወተው የግሪክ ብሔራዊ ቡድን በጥልቅ ሃዘን ባልዶክን ተሰናብተናል ማለቱንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ተጫዋቹ ለሀገሩ ብሔራዊ ቡድን ለመጨረሻ ጊዜ የተጫወተው በመጋቢት 2024 ሀገሩ ግሪክ ከጆርጅያ ጋር ባደረገችው ጨዋታ ነው፡፡
የግሪክ እግር ኳስ ማኅበረሰብ በድንጋጤ ውስጥ መኾኑም ተነግሯል፡፡ የባልዶክ ድንገተኛ ሞት ዜና ሀገሪቱን በሃዘን ውስጥ እንዳስገባትም ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል፡፡ ዛሬ ምሽት በሀዘን ውስጥ ኾኖ ወደ ሜዳ የሚገባው የግሪክ ብሔራዊ ቡድን ጥቁር አርማ አድርጎ እንደሚገባም ይጠበቃል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!