የአውሮፓ አሸናፊዎች አሸናፊ ምሽት ይከናወናል።

0
231

ባሕር ዳር: ነሐሴ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊውን ከኢሮፓ ሊግ አሸናፊው የሚያገናኘው የአውሮፓ አሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታ ዛሬ ምሽት ይደረጋል፡፡ በእንግሊዝ ዌንብሌይ የጀርመኑ ቦርሲያ ዶርትመንድን አሸንፎ ለ15ኛ ጊዜ ዋንጫ ከፍ ያደረገው የዓለማችን ኀያሉ ቡድን ሪያል ማድሪድ ከጣሊያኑ አትላንታ ጋር የአህጉሩን የአሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታን ያደርጋል፡፡

በአውሮፓ ምድር ከሁሉም ክለቦች ልቆ የአህጉሪቱን ትልቁን ዋንጫ የሠበሠበው ሪያል ማድሪድ ሌላ ዋንጫ ከፍ ለማድረግ ዛሬ ምሽት ይጫወታል፡፡ ፈረንሳዊውን ኮከብ ኪሊያን ሜባፔ ወደ ክለቡ የቀላቀለው ማድሪድ በአዲሱ የውድድር ዘመን ካለፈው ዓመት የላቀ አስፈሪ እንደሚኾን ይገመታል፡፡
ሌላኛው አዲስ ተጫዋች ብራዚላዊው ኢንድሪክም የማድሪድን አስፈሪነት ከሚጨምሩ ተጫዋቾች መካከል አንደኛው ነው፡፡

አዲሱ የቡድኑ ኮከብ ኪሊያን ሜባፔ ዛሬ የመጀመሪያውን ጨዋታ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡ አሠልጣኝ ካርሎ አንቾሎቲም አዲሱ ኮከባቸው ለጨዋታው ዝግጁ መኾኑን መናገራቸውን ኢ ኤስ ፒኤን ዘግቧል፡፡ ሪያል ማድሪድ ተደጋጋሚ ጊዜ ያሸነፈውን ዋንጫ ለማሸነፍ ወደ ሜዳ ሲገባ አትላንታ ለአውሮፓ ሱፐር ካፕ ዋንጫ ጨዋታ የመጀመሪያው መኾኑን ናይንቲ ሚኒት ዶት ኮም ዘግቧል፡፡

የጀርመኑን ባየር ሊቨርኩሰንን 3 ለ 0 በማሸነፍ የአውሮፓ ሊግ ዋንጫን ያሸነፈው አትላንታ በታሪኩ የመጀመሪያ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫውን ለማሳካት ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል፡፡ የጂያን ፔሮ ጋስፔሪኒው አትላንታ በዓመቱ በሁሉም ውድድሮች ምንም ሽንፈት ሳይገጥመው ለፍጻሜ የደረሰውን ሌቨርኩሰንን ድል በማድረግ ዋንጫውን የወሰደበት የፍጻሜ ጨዋታ አድናቆትን አስችሮታል፡፡

በፍጻሜው ጨዋታ ናይጀሪያዊው አጥቂ ሉክማን ሦስት ግቦችን በማስቆጠር ሀትሪክ ሠርቷል፡፡ አትላንታ ያሳካው ዋንጫ ከ61 ዓመታት በኋላ የተገኘ ነበር፡፡ ዛሬ ድል ካደረገ ደግሞ ለጣሊያኑ ክለብ ሌላ ደስታ እና ክብር ይኾናል፡፡ ስፖርቲንግ ኒውስ በዘገባው ሪያል ማድሪድ ዛሬ ዋንጫውን የሚያሳካ ከኾነ የአውሮፓ ሱፐር ካፕ ዋንጫን ብዙ ጊዜ በማሸነፍ ብቸኛው ክለብ ይኾናል ብሏል፡፡

የአትላንታው አጥቂ ሉክማን ዛሬም ለቡድኑ አዲስ ነገር ሊሰጥ እንደሚችል ስፖርቲንግ ኒውስ አስነብቧል፡፡ የአውሮፓ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ (ሱፐር ካፕ) የአውሮፓን አሸናፊ ቡድን ለመለየት ሲደረግ፣ የአዲሱ የውድድር ዘመን ትዕይንት ማሳያ እንደ መጋረጃ መክፈቻ ተደርጎም ይወሰዳል፡፡ አዲሱ የውድድር ዘመን እንደ ቲያትር እና መድረክ ሲቆጠር የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ደግሞ እንደ መጋረጃ መግለጫ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡

የ2022 የአውሮፓ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ባለ ድሉ ማድሪድ በ2024 ለሌላ ዋንጫ ይጫወታል፡፡ የ2023 የአውሮፓ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ የእንግሊዙ ማንቸስተር ሲቲ ማሸነፉ ይታወሳል፡፡ ዛሬ በሚደረገው ጨዋታ ፈረንሳዊው የማድሪድ አማካይ ኢድዋርዶ ካማቪንጋ እና ዴቪድ አላባ በጉዳት ምክንያት ጨዋታው ያልፋቸዋል ተብሏል፡፡

በአትላንታ በኩል አጥቂው ጃኑሉካ ሳካማካ በጉዳት ምክንያት ጨዋታው ያልፈዋል ነው የተባለው፡፡ የማድሪዱ አማካይ ካማቪንጋ ከስድስት እስከ ሰባት ሳምንታት ከሜዳ ሊርቅ እንደሚችልም ተዘግቧል፡፡ ጨዋታው ምሽት 4፡00 በፖላንድ ይካሄዳል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here