ባሕር ዳር: ነሐሴ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሪያል ማድሪድ በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ በ2023/24 የውድድር ዘመን የቡንደስሊጋውን ክለብ ዶርትሙንድን በዌምብሌይ 2 ለ 1 አሸንፎ 15ኛ ዋንጫውን ወደ ካዝናው ማስገባቱ ይታወሳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በስፔን ላሊጋ 36 ዋንጫዎችን በመሠብሠብ 27 ዋንጫዎችን ካሳካው ባርሴሎና በዘጠኝ ዋንጫዎች በልጦ ተቀምጧል፡፡
ሎስ ብላንኮዎቹ በአዲሱ የውድድር መርሐ ግብር በላሊጋው ከሚያደርጉት እልህ አስጨራሽ ፉክክር በተጨማሪ ከአታላንታ ጋር የአውሮፓ አሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታ እና በዓለም የክለቦች ዋንጫ ላይም ይሳተፋሉ፡፡ የፈረንሳዩን አምበል ኪሊያን ምባፔን ከፒ ኤስ ጂ ያስፈረሙት ሪያል ማድሪዶች የአጥቂ መሥመራቸው በምባፔ፣ ቪንሸስ ጁኒየር፣ ጁዲ ቤሊንግሃም እና ሮድሪጎ የሚመራ በመኾኑ ለየትኛውም ክለብ የተከላካይ መሥመር ሥጋት እንደሚኾኑ የቢቢሲ ስፖርት መረጃ ይጠቁማል፡፡
በዚህ ሥብሥብ ውስጥ የ18 ዓመቱ ብራዚላዊ ወጣት አጥቂ ኤንድሪክ ሲጨመርበት ማድሪድን ከግሥጋሴው ማን ያስቆመዋል? የሚለውን ጥያቄ ያጭራል፡፡ እንደ አርዳ ጉለር ያሉ ወጣት ተስፈኞችም የሎስ ብላንኮዎቹ የጥንካሬ ምሰሶዎች እንደሚኾኑ ይጠበቃል፡፡ በማድሪድ ቤት ውስጥ በውጤት ያሸበረቁት አንጋፋው ጣሊያናዊ አሠልጣኝ ካርሎ አንቼሎቲ በነጮቹ ቤት ሊፈተኑ ይችላሉ ተብሎ የተገመተው እነማንን ቋሚ ተሰላፊዎች ያደርጋሉ? እነማንንስ ተጠባባቂ ወንበር ላይ ያስቀምጣሉ? በሚለው ጥያቄ እንደኾነም ተገምቷል፡፡
ባርሴሎና እና አትሌቲኮ ማድሪድ በ2024/25 የላሊጋ ፉክክር ላይ ሌሎቹ የከባድ ሚዛን ተፋላሚዎች ይኾናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ባርሴሎናዎች ዣቪ ሄርናንዴዝን አሰናብተው የቀድሞውን የባየር ሙኒክ እና የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ሃንስ ፍሊክን ወደ ክለባቸው ቀላቅለዋል፡፡
የካታላኑ ክለብ ከአሠልጣኙ ለውጥ በተጨማሪ በአውሮፓ ዋንጫ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ኾኖ ያጠናቀቀውን ስፔናዊውን ዳኒ ኦልሞን ከጀርመኑ አር ቢ ሌብዚዥ ወደ ክለቡ ቀላቅሏል፡፡ ባርሳዎች በአዳዲስ ተጨዋቾች ግዥ ላይ ብዙም ተሳትፎ ያላደረጉ ቢኾንም በአውሮፓ ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ በ16 ዓመቱ ደምቆ የታየው ያሚን ያማል በዘንድሮው የባርሴሎና ክለብ ውስጥ ሚናው ይጎላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ያማል በጀርመኑ የአውሮፓ ዋንጫ ወጣት ኮከብ ተጨዋች ተብሎ መመረጡ ይታወቃል፡፡
የካታላኑ ክለብ ከያማል በተጨማሪ የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊዎቹ ፌርሚን ሎፔዝ እና ፓኡ ኩባርሲም በክለቡ ውስጥ የሚኖራቸው ሚና በጉልህ የሚጠበቅ ነው ሲል ቢቢሲ ስፖርት ግምቱን አስቀምጧል፡፡ የአትሌቲኮ ማድሪዱ አርጀንቲናዊ አሠልጣኝ ዲያጎ ሲሞኒ ባለፈው ዓመት በላሊጋው አራተኛ ኾነው ያጠናቀቁበት ውጤታቸው ደስተኛ አላደረጋቸውም፡፡
የስፔኑን የመሐል ተከላካይ ሮቢን ሊ ኖርማንድ፣ የኖርዌዩን አጥቂ አሌክሳንደር ሶርሎዝ እና አርጀንቲናዊውን የማንቸስተር ሲቲ የአጥቂ መሥመር ተጨዋች ጁሊያን አልቫሬዝን በክለባቸው የያዙት አትሌቲኮ ማድሪዶች የከተማቸውን ተቀናቃኝ ሪያል ማድሪድንም ኾነ ባርሴሎናን በመብለጥ በላሊጋው ክብርን ለመቀዳጀት ይፋለማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
እንግሊዛዊው የቼልሲ የአጥቂ አማካይ ኮኖር ጋላቸርም ሌላኛው የአትሌቲኮ ማድሪድ አቅም ይኾናል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ በዘንድሮው የስፔን ላሊጋ ሦስቱ ፈረሶች ለዋንጫ የሚያደርጉት ግልቢያ በጉጉት የሚጠበቅ ሲኾን ሌሎች ክለቦችም በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ለመሳተፍ በሚያደርጉት ብርቱ ፉክክር የላሊጋው ድምቀት ይኾናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!