የኢትዮጵያን ስም በዓለም ዓደባባይ ከፍ በሚያደርገው የአትሌቲክስ ስፖርት ላይ የሚታየዉን ክፍተት በውል በመረዳት ማስተካከል እንደሚገባ ርእሰ ብሔር ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

0
269

አዲስ አበባ: ነሐሴ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዚህ የእዉቅና እና ሽልማት መርሐ ግብር ርዕሰ ብሔር ሳህለወርቅ ዘዉዴ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ተገኝተዉበታል። ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ስፖርት በዓለም የምትጠበቅ ሀገር መኾኗን ያነሱት ርዕሰ ብሔሯ በፓሪስ ኦሎምፒክ ተሳትፎ ያደረጉና ዉጤት ያመጡ አትሌቶች፣ አሠልጣኞች፣ አመራሮች እንዲሁም ከስፖርቱ ጎን ለተሠለፉት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

ሜዳሊያ ያመጡ አትሌቶች ሀገራችሁን ስላኮራችሁ ደስ ብሎናል ያሉት ርዕሰ ብሔሯ በታምራት ቶላ እና ሲሳይ ለማ መካከል የታየዉ የሀገር ክብር ስሜት እና ፍቅር ብዙ የምንማርበት ነዉ ሲሉ ገልጸዋል። ሲሳይ ለምን ፈረንሳይ እንደደረሰ በቅጡ የገባዉ ሀገር ወዳድ መኾኑንም ነዉ የተናገሩት። ርዕሰ ብሔር ሳህለወርቅ የብር ሜዳሊያ ያስገኙት ትዕግስት አሰፋ፣ ጽጌ ድጉማ እና በሪሁ አረጋዊ ለሀገር ላበረከቱት እና ላደረጉት ጥረት እዉቅና ሰጥተዋል።

እንደ ሀገር በኦሎምፒክ ስፖርት ከጊዜ ወደ ጊዜ ዉጤታችን አመርቂ አለመኾኑን አስመልክቶ ባነሱት ሐሳብም በቶኪዮ ኦሎምፒክ የነበረዉን ክፍተት አስመልክተዉ በወቅቱ የሰጡትን ሐሳብ በማስታወስ አሁንም ስፖርቱ ላይ የሚታየዉን ክፍተት በውል በመረዳት ሊስተካከል እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሕዝቡ አስተያየት ምንድን ነዉ? የሚለዉ ጉዳይ በጥልቀት ሊጤንበት እንደሚገባም ነዉ የጠቆሙት። ወቅቱን የዋጀ ጊዜዉን የሚመጥን አሠራር መዘርጋት እንዳለበትም በንግግራቸዉ አስገንዝበዋል።

በዚሁ የእዉቅና ሽልማት መርሐ ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት የባሕልና ስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ አትሌቶች በኦሎምፒክ መድረክ የሀገራቸዉን ሰንደቅ ከፍ ለማድረግ ያደረጉትን ጥረት አድንቀዋል። ሚኒስትሯ በኢትዮጵያ ስፖርት ላይ እንቅፋት የኾኑትን የአሠራር እና የሕግ ማዕቀፎች በማስተካከል ኢትዮጵያ ወደ ቀደመ ዝናዋ ለመመለስ እንደሚሠራም ጠንከር ያለ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዚሁ መድረክ የተገኙት የኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ሐሳባቸዉን ሲሰጡ የዉጤት መጥፋቱን ምክንያት ከእርሳቸዉ ባራቀ መንገድ ነበር። እንደ ምክንያትነትም ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሌላት መኾኑ ዉጤት እንዳናመጣ አድርጎናል ሲሉ ተሰምተዋል። አያይዘዉም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ላይ አሠልጣኝ ሳይኾን የአትሌቶች አሠልጣኝ የሚመረጥበት አካሄድ እየተከተልን ነዉ ብለዋል።

ዶክተር አሸብር ለኢትዮጵያ ዉጤት ማጣት ሌላኛዉ ምክንያት ኢትዮጵያውያን በምንታወቅበት ርቀቶች ላይ እነ ኖርዌይ፣ አሜሪካና የመሳሰሉ ሀገራት ጠንክረዉ መገኘት ከአሁን ቀደም እንደነበረዉ ዉድድሩ በኬኒያ እና በኢትዮጵያ ብቻ አለመኾኑን አንስተዋል። ዉጤቱ እንኳን ለሕዝቡ ይቅርና እኛም ያልጠበቅነዉ ነዉ ብለዋል። የኦሎምፒክ ፕሬዚዳንቱ በአቀባበል ፕሮግራሙ ካነሡት ሐሳብ አንድም ስህተት ወደራሳቸዉ ሲያስጠጉ አላየንም።

በብሔራዊ ቤተ መንግሥት በነበረዉ የእዉቅናና ሽልማት ሥነ ስርዓት ለተሳታፊ አትሌቶችና አረልጣኞች ከ50 ሺህ እስከ 7 ሚሊዮን ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። አትሌት ቀነኒሳ በቀለ 50 ግራም የወርቅ ኒሻን ለሜቻ ግርማ ደግሞ 2 ሚሊዮን ብር በልዩ ተሸላሚነት ተበርክቶላቸዋል። የብር ሜዳሊያ ያገኙ አትሌቶች 4 ሚሊዮን ብር ሲሸለሙ የወርቅ ሜዳሊያ ያመጣዉ ታምራት ቶላ የ7 ሚሊዮን ብር ሽልማት ተበርክቶለታል።

በዚህ የሽልማት መርሐ ግብር አሠልጣኝ ገመዶ ደደፎ የ2 ሚሊዮን ብር ሽልማት የተበረከተለት ሲኾን የተሸለምኩት ብር ያንሰኛል በማለት ሽልማቷን መልሷል። በአጠቃላይም ለሽልማት 25 ሚሊዮን ብር ወጭ መደረጉ ተሰምቷል። ኢትዮጵያ በፓሪስ ኦሎምፒክ በአንድ ወርቅና በሦስት ብር ሜዳሊያወች ከዓለም 47ኛ ከአፍሪካ አራተኛ ኾና ማጠናቀቋ የሚታወስ ነዉ።

ዘጋቢ፡- ቴዎድሮስ ኃይለኢየሡስ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here