ጥቁር አሠልጣኞች በእንግሊዝ ፕርምየር ሊግ ታሪክ።

0
187

ባሕር ዳር: ነሐሴ 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ብዙ ተመልካች አለው በሚባለው የእንግሊዝ ፕርምየር ሊግ ውስጥ ጥቁር አሠልጣኞችን ማየት ብዙም የተለመደ አይደለም፡፡ በእንግሊዝ ፕርምየር ሊግ ውስጥም ኾነ በእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ግን በርካታ የቆዳ ቀለማቸው ጥቁር የኾኑ ተጨዋቾች ተጫውተው አልፈዋል፤ አሁንም በመጫወት ላይ ይገኛሉ፡፡

ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ተቋም (ፊፋ/ ጨምሮ ሌሎችም ሀገራት ዘረኝነትን ከእግር ኳስ ሜዳ ለማራቅ ጥረት ሲያደርጉ ቢስተዋልም፣ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቷል ማለት ግን ያዳግታል፡፡ ለዚህ እሳቤ አስረጂ የሚኾነው ደግሞ በአውሮፓ ትላልቅ በሚባሉት የስፔን፣ የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ፣ የጣሊያን እና የጀርመን ሊጎች ውስጥ ዘረኝነት በየደረጃው የሚንጸባረቅ መኾኑ ነው፡፡

በእንግሊዝ ፕርምየር ሊግ ውስጥ ምንም እንኳን በርከት ያሉ ጥቁር አሠልጣኞችን ማየት ባይቻልም ጥቂት ጥቁር አሠልጣኞች ግን በሊጉ ውስጥ አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡ ጎል ዶት ኮም በእንግሊዝ ፕርምየር ሊግ በዋና አሠልጣኝነት የተሳተፉ ጥቂት አሠልጣኞችን በዚህ መልኩ ያስታውሳቸዋል፡፡ በእንግሊዝ ፕርምየር ሊግ የጀመሪያው ጥቁር አሠልጣኝ ሩድ ጉሌት ነው፡፡ ኔዘርላንዳዊው የእግር ኳስ ጥበበኛ የምዕራብ ለንደኑን ቼልሲ በ1996 (እ.ኤ.አ) አሠልጥኗል፡፡

በተጨዋችነት ዘመኑ በኤስ ሚላን፣ ፒ ኤስ ቪ እና በኔዘርላንድ ብሔራዊ ቡድን ምርጥ ጊዜን ያሳለፈው ጉሌት ከቼልሲ በመቀጠል በ1998/99 ኒውካስትልን አሠልጥኗል፡፡ አየርላንዳዊው ክሪስ ሁተንም እንደ ሩድ ጉሌት ሁሉ በእንግሊዝ ፕርምየር ሊግ ውስጥ ከአንድ በላይ ክለብ ያሠለጠኑ ጥቁር አሠልጣኝ ናቸው፡፡ ክሪስ ሁተን ኒውካስትል ዩናይትድን፣ ኖርዊች ሲቲን እና ከቅርብ ዓመታት በፊት ደግሞ ብራይተንን አሠልጥነዋል፡፡

እንግሊዛዊው ፖል ኢንስ ጥቁር እንግሊዛዊ ኾኖ ብላክበርን ሮቨርስን ያሠለጠነ የመጀመሪያው ሰው ኾኗል፡፡ በሊቨርፑል መለያ ብዙ ታሪክ የጻፈው ፖል ኢንስ የብላክበርን አሠልጣኝ መኾኑ ብቻ ሳይኾን የመጀመሪያው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አምበል ኾኖም ተጫውቷል፡፡ ፈረንሳይን ባለ ድል ባደረገው የ1984 አውሮፓ ዋንጫ ላይ ደምቆ የታየው ጥቁሩ ኮከብ ጂን ቲጋና በእንግሊዝ ፕርምየር ሊግ የፉልሃም አሠልጣኝ ኾኖ ሠርቷል፡፡

ፖርቱጋላዊው ኑኖ ስፕሪቶ ሳንቶ ዎልቨር አምፕተንን ከእንግሊዝ የታችኛው ሊግ ወደ ፕርምየር ሊጉ በማሳደግ ያሠለጠኑ ሲኾን በ2019/20 የውድድር ዘመን ዎልቭስን ለኢሮፓ ሊግ ተሳትፎ በማብቃታቸውም ይታወሳሉ፡፡ ኑኖ ስፕሪቶ ሳንቶ የቶተንሃም አሠልጣኝ ኾነውም ሠርተዋል፡፡ ጃማይካዊው ዳረን ሙር በእንግሊዝ ፕርምየር ሊግ ዌስትብሮምን ያሠለጠኑ ብቸኛው ጥቁር እና ጃማይካዊ አሠልጣኝ ናቸው፡፡

የቀድሞው የአርሰናል ተጨዋች እና አምበል ፈረንሳዊው ፓትሪክ ቪዬራ ክሪስታል ፓላስን ከ2021 እስከ 2023 ለሁለት ዓመታት ያሠለጠነ ሌላኛው ጥቁር አሠልጣኝ ነው፡፡ የማንቸስተር ሲቲ ተጨዋች እና አምበል የነበረው ቤልጅየማዊው ቪሰንት ኮምፓኒ በርንሌይን በ2022/23 ከታችኛው ሊግ አሳድጎ በ2023/24 በፕርምየር ሊጉ አሠልጥኗል፡፡ ቪሰንት ኮምፓኒ አሁን ላይ የባየር ሙኒክ አሠልጣኝ ኾኖ ወደ ጀርመን ማቅናቱ የሚታወቅ ነው፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጥቁር ተጨዋቾች ወደ አሠልጣኝነቱ ሙያ እየተቀላቀሉ መምጣታቸው በጥሩ ጎኑ የሚታይ ቢኾንም ከችሎታ እና ከዕውቀት ባሻገር ለቆዳ ቀለም ቅድሚያ የሚሰጡ የክለብ ባለቤቶች እና የእግር ኳስ አሥተዳዳሪዎች ደጋግመው የሚያሥቡበት ጊዜ ላይ ተገኝተናል፡፡

እንደ ፈረንሳይ እና እንግሊዝ ያሉ ሀገራት በጥቁር ተጨዋቾቻቸው ደማቅ ታሪክ የመጻፋቸውን ያህል ጥቁር አሠልጣኞችን የመግፋት የዘረኝነት እሳቤያቸውንም አሽቀንጥረው እንዲጥሉት ይጠበቃል፡፡ ለዚህ ጥሩ ጅምር ማሳያ የሚኾነው ደግሞ በቅርቡ በተጠናቀቀው የፓሪስ ኦሎምፒክ ላይ የፈረንሳይን የኦሎምፒክ የእግር ኳስ የወንዶች ቡድን የመራው ጥቁሩ ቴሪ ዳንኤል ሆነሪ መኾኑ ነው፡፡

ዘረኝነት ከእግር ኳስ ሜዳ እየራቀ በሄደ ቁጥር በተጨዋችነታቸው የዓለም እግር ኳስ ወዳድ ሕዝብን ያስደመሙት ጥቋቁር ከዋክብት በአሠልጣኝነቱም ውጤታማ የማይኾኑበት ምክንያት የለም፡፡

ዘጋቢ፡- እሱባለው ይርጋ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here