የማንቸስተር ሲቲን ኀያልነት የሚያስቆም ይኖር ይኾን?

0
183

ባሕር ዳር: ነሐሴ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ነሐሴ 10/2016 ዓ.ም አርብ ምሽት 4 ሰዓት ላይ ማንቸስተር ዩናይትድን ከፉልሃም ጋር በሚያገናኘው ጨዋታ ይጀምራል፡፡ ከዚህ ጨዋታ ቀደም ብሎ ደግሞ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊው ማንቸስተር ሲቲ እና የእንግሊዝ ኤፍ ኤ ዋንጫ አሸናፊው ማንቸስተር ዩናይትድ በአሸናፊዎች አሸናፊ (ኮሚኒቲ ሺልድ) ጨዋታ ቅዳሜ በ04/12/2016 ዓ.ም ከቀኑ 11፡00 ሰዓት ላይ የደርቢ ፍልሚያቸውን ያደርጋሉ፡፡

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ2024/25 ውድድር ሲጀምር የብዙዎች ጥያቄ “ማንቸስተር ሲቲን ማን ከግስጋሴው ያስቆመዋል?” የሚለው እንደኾነ ቢቢሲ በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡ ስፔናዊው አሠልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ማንቸስተር ሲቲን ማሠልጠን ከጀመሩ ጊዜ አንስቶ ስድስት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎችን አሳክተዋል፤ ለአራት ተከታታይ ዓመታት በማሸነፍ ደግሞ አዲስ ክብረ ወሰን ጽፈዋል፡፡

ቢቢሲ ባለፈው ዓመት ከ2ኛ እስከ 8ኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁ ክለቦች ምን ያህል ሲቲን ሊገዳደሩት ይችላሉ? ሲል ይጠይቃል፡፡ አርሰናል፡- ባለፈው ዓመት ከሻምፒዮናው ማንቸስተር ሲቲ በ 2 ነጥብ ብቻ ዝቅ ብሎ ዋንጫውን ሳያሳካ ቀርቷል፡፡ ባለፉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት የማንቸስተር ሲቲ ተፎካካሪ እና ተከታይ የነበረው የሰሜን ለንደኑ አርሰናል ነው፡፡

አርሰናል ለ2024/25 የውድድር ዘመን ጣሊያናዊውን የቦሎኛ የተከላካይ መስመር ተጫዋች ሪካርዶ ካላፊዮሪን አስፈርሟል፡፡ በአርሰናል ሁለቱ ያለፉት ዓመታት የክለቡ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ እንግሊዛዊው ቡካዮ ሳካ ነው፡፡ የክለቡ አምበል ማርቲን ኦዲጋርድ ”በቀጣይ ዓመት የምንጫወተው ለዋንጫ ብቻ ነው“ ሲል ተደምጧል፡፡

ሊቨርፑል፡- ባለፈው ዓመት ከማንቸስተር ሲቲ በ 9 ነጥብ ርቀው በ3ኛ ደረጃ አጠናቅቀዋል፡ጀርመናዊውን ስኬታማ አሠልጣኝ ጀርገን ክሎፕን በአርኔ ስሎት የቀየሩት ቀዮቹ ማንቸስተር ሲቲ በ 7 ዓመት ውስጥ 6 ዋንጫዎችን ሲያሳካ አንዱን ዋንጫ የወሰዱት እነሱ ናቸው፡፡ አርኔ ስሎት በክሎፕ የተገነባ ጥሩ ቡድን ቢኖራቸውም በመጀመሪያ ዓመት ውድድራቸው ሲቲን ይፎካከራሉ ወይም ዋንጫ ይስማሉ ተብሎ እንደማይጠበቅ ተገምቷል፡፡

አስቶን ቪላ፡- ከማንቸስተር ሲቲ በ23 ነጥብ ርቀው የ4ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቅቀዋል፡፡ በኡናይ ኤምሬ እየተመሩ የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎን ያሳኩት ቪላዎች፣ አማዱ ኦናናን ከኤቨርተን፣ ኢያን ማትሰንን ከቼልሲ እና ሮዝ ባርክሌይን ከሉተን ወደ ሥብሥባቸው ቀላቅለዋል፡፡ ቪላዎች ብራዚላዊውን ዳግላስ ሉዊዝ እና ፈረንሳዊውን ሙሳ ዲያቢ ከክለባቸው በመልቀቃቸው እንዳይቸገሩም ሥጋት ተፈጥሯል፡፡

ቶተንሃም ሆትስፐር፡- ከማንቸስተር ሲቲ በ25 ነጥቦች ዝቅ ብለው በ5ኛ ደረጃ አጠናቅቀዋል፡፡ ቶተንሃሞች በአሠልጣኝ ኤንጂ ፖስትኮግሉ እየተመሩ የቆዩ ቢኾንም የመጨረሻ ውጤታቸው ግን በተጠበቁት ልክ አይደለም፡፡ ፖስትኮግሉ ቶተንሃም በቀጣይ ዓመት የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎን ለማግኘት እና ከዚያም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡

ቼልሲ፡-ባለፈው ዓመት ከማንቸስተር ሲቲ በ28 ነጥብ ዝቅ ብለው በ6ኛ ደረጃ ጨርሰዋል፡፡ ሰማያዊዎቹ ሌስተር ሲቲን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያሳደጉትን ኤንዞ ማሬስካን በማውሪሲዮ ፖቺቲኖ ተክተዋል፡፡ ማሬስካ ጥሩ ሥብሥብ አለው የተባለውን ቼልሲ እየመሩ በኢሮፓ ሊግ እና በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጥሩ ውጤት ያስመዘግባሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡

ኤንዞ ማሬስካ ከአርጀንቲናዊው ኤንዞ ፈርናንዴዝ ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ችግርም ክለቡን በማይጎዳ መልኩ ይቀርፉታል ተብሎም ታስቧል፡፡ ኒውካስትል ዩናይትድ፡- ከማንቸስተር ሲቲ በ31 ነጥብ ዝቅ በማለት በ7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ በ2022/23 የውድድር ዘመን ሳይጠበቁ የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ የኾኑት ኒውካስትሎች በ2023/24 የውድድር ዘመን በተጠበቁት ልክ አልተጓዙም፡፡

በኤዲ ሆው የሚመሩት ኒውካስትሎች አዳዲስ ተጨዋቾችን ወደ ክለባቸው ለመቀላቀል የግዴታ ተጨዋቾችን ከክለባቸው ማሰናበት ይኖርባቸዋል፡፡ በኒውካስትል ቤት እንደ ጥሩ ነገር እየተነሳ ያለው እስካሁን ድረስ በብዙ ክለቦች የሚፈለጉትን አሌክሳንደር አይዛክ፣ ቡሩኖ ጉማሬሽ እና አንቶኒ ጎርደንን አለመሸጣቸው ነው፡፡

ማንቸስተር ዩናይትድ፡-ከማንቸስተር ሲቲ በ31 ነጥብ ዝቅ ብለው በ8ኛ ደረጃ ጨርሰዋል፡፡ ቀያይ ሰይጣኖቹ ከ1989/90 በኋላ ዝቅተኛውን የ8ኛ ደረጃ ያስመዘገቡበት ጊዜ አልነበረም፤ ያም ኾኖ ግን የኤፍ ኤ ዋንጫ ባለ ድል በመኾናቸው የኢሮፓ ሊግ ተሳታፊ መኾን ችለዋል፡፡ ባስመዘገቡት ዝቅተኛ ውጤት ምክንያት ከክለቡ ይሰናበታሉ ተብሎ የተገመቱት ኔዘርላንዳዊው ኤሪክ ቴን ሃግ ከክለቡ ጋር ለሁለት ዓመት እንዲቆዩ ተፈቅዶላቸዋል፡፡

ቀያይ ሰይጣኖቹ የቦሎኛውን አጥቂ ጆሹዋ ዚርኪዝ እና የሊሉን የመሐል ተከላካይ ሌኒ ዮሮን ወደ ክለባቸው ቀላቅለዋል፡፡ ራፋኤል ቫራን እና አንቶኒ ማርሻልን በነጻ የለቀቁት ማንቸስተር ዩናይትዶች ሌሎች አዳዲስ ተጨዋቾችን ወደ ክለባቸው በመቀላቀል ወደ ቀደመ ዝናቸው ለመመለስ እንደሚጥሩም ተገምቷል፡፡

ለአራት ተከታታይ ዓመታት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ያሳኩት ፔፕ ጋርዲዮላ እና ሠራዊታቸው ዘንድሮም ለዋንጫው የተሻለ ግምት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ማንቸስተር ሲቲዎች ብዙ የመሰለፍ ዕድል አላገኘሁም ያለውን አርጀንቲናዊ ጁሊያን አልቫሬስን ለአትሌቲኮ ማድሪድ ከመሸጣቸው በቀር ዋንጫ ያስገኘላቸው ሥብሥባቸውን አሁንም እንደያዙ ናቸው፡፡

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሳምንት ብቻ ቀርቶታል። የብዙዎች ጥያቄም ማንቸስተር ሲቲን ማን ያስቆመዋል የሚለው ነው? እርስዎስ ማንቸስተር ሲቲን ማን ያስቆመዋል ብለው ይገምታሉ?

ዘጋቢ፡- እሱባለው ይርጋ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here