ባሕር ዳር: ሐምሌ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከትምህርት ቤቶች የስፖርት ውድድር ተነስተው ለትልቅ ድል እና ዝና የበቁ በርካታ አትሌቶች አሉ፡፡ በ33ኛው የፓሪስ ኦሎምፒክ እየተሳተፉ ከሚገኙ አትሌቶች ውስጥ ደግሞ የታላቋ ብሪታኒያ የመካከለኛ ርቀት ሯጭ የኾነችው ጆርጂያ ቤል ማስተርሷን የያዘች ወጣት ነች፡፡
የ24 ዓመቷ ካምሪን ሮጀርስም በፓሪስ ኦሎምፒክ የመዶሻ ወርዋሪ አትሌት ስትኾን የማስተርስ ዲግሪ ባለቤትም ናት፡፡ ስዊድናዊቷ የዲስከስ ወርዋሪ ካሲያ ማሪዬ ሊንድሎፍ ሌላኛዋ ባለ ማስተር አትሌት ናት፡፡ የ23 ዓመቷ ካናዳዊቷ ሲንዲ ኮሊንስም ለካናዳ ሴቶች እግር ኳስ ተመርጣ ወደ ፓሪስ ካቀናች በኋላ ጉዳት አጋጥሟታል፤ ያም ኾኖ ግን ሲንዲም ባለማስተርስ አትሌት ናት፡፡
እነዚህ አራቱ ባለማስተርስ አትሌቶች የበርክሌይ ዩኒቨርሲቲ ፍሬዎች መኾናቸውን ዩኒቨርስቲው በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስነብቧል፡፡ የዩኒቨርሲቲው አስተማሪ ፕሮፌሰር ደርክ ቫን ሬነን በተማሪዎቻቸው አትሌትነት እና የተማሩ አትሌቶች በመኾናቸው እንደሚኮሩ ገልጸዋል፡፡
ፕሮፌሰሩ አራቱም ምሁር አትሌቶች ሴቶች በመኾናቸው ደግሞ የበለጠ ኩራት እንደሚሰማቸውም ነው የገለጹት፡፡ እነዚህ አትሌቶች የስፖርት ፋላጎት ላላቸው ታዳጊዎች በስፖርትም በትምህርትም ጎን ለጎን ውጤታማ እንደሚኮን ማስተማሪያ ናቸው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!