የ5ሺህ ሜትሯ ንግስት!

0
197

ባሕር ዳር: ሐምሌ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ5 ሺህ ሜትር የምንጊዜም ድንቅ ተብለው ከሚዘከሩ አትሌቶች አንዷ ናት። በኦሎምፒክ ለሀገሯ ሁለት የወርቅ ሜዳልያ ያስገኘች የሀገር ባለውለታ ስትኾን በጊዜዋ የክብረወሰን ባለቤትም ጭምር ናት። በ3 ሺህ ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር በተከታታይ አራት ጊዜ ባለድል በመኾን ብቸኛዋ እንስት ናት- መሰረት ደፋር።

ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ኦሎምፒክ በአቴንስ ነበር የተካሄደው። በወቅቱ ኢትዮጵያ 2 ወርቅ፣ 3 ብር እና 2 ነሀስ በድምሩ 7 ሜዳልያ አስመዝግባለች። የተገኙት ሁለቱ ወርቆች በቀነኒሳ በቀለ እና መሰረት ደፋር የተመዘገቡም ነበሩ። ቀነኒሳ በ10 ሺህ፣ መሰረት ደፋር ደግሞ በ5 ሺህ የደመቁበት ጊዜ ነው።

መሰረት ደፋር ከአቴንሱ ኦሎምፒክ በፊት በ3 እና 5 ሺህ ሜትሮች አሸናፊ በመኾን አቅሟን አሳይታለች። ነገር ግን የዓለምን ትኩረት የሳበችው በአቴንሱ ኦሎምፒክ በ5 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ባለቤት በመኾኗ ነው። ከዚህ ድል በኋላ መሲ የ5 ሺህ ሜትር ምርጧ ሯጭ መኾኗን በተለያዩ ውድድሮች አሳየች። 14 ደቂቃ፣ 24 ሴኮንድ ከ53 ማይኮሮ ሴኮንድ በመግባት የ5 ሺህ ሜትር ክብረወሰንን መያዟ ለዚህ ማሳያ ነው ይላል የወርልድ ፕረስ ዘገባ።

“እኔ ለሩጫ ነው የተፈጠርኩት” የምትለው መሰረት በ2012 የለንደን ኦሎምፒክ 5ሺህ ሜትሩን ዳግም ደምቃበታለች። በሴቶች 5ሺህ ሜትር መሰረት ደፋር በኦሎምፒክ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ለሀገሯ በማበርከት በኩራት ለትውልድ የሚነገር ታሪክ ሠርታለች። ትናንት በወርቃማ የሩጫ ዘመኗ እንዲህ ሀገር ያኮራችው መሰረት ለዛሬዎቹ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ወካዮች ብርታት ናት። ዛሬ ታሪክ ለመጻፍ ለተዘጋጁት የትናንቶቹ አሸናፊነት ስንቅ ነው እና፤ የመሲ 5ሺህ ሜትር ትልቅነት ለእነ ጉዳፍ ማሸነፍ ብርታት ይኾናል።

ድል ለኢትዮጵያውያን!

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here