ባሕር ዳር: ሐምሌ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በረዥም ርቀት ከታዩ የዓለም ምርጥ አትሌቶች መካከል ቀነኒሳ በቀለ ከግንባር ቀደምቶች አንዱ ነው። ብዙዎች ስለመጨረሻ ዙር አጨራረሱ እና የአሯሯጥ መንገዱ ማራኪነት ብዙ ብለውለታል። በዘንድሮው የፓሪስ ኦሎምፒክ ሀገሩን በማራቶን የሚወክለው ቀነኒሳ ሀገርን ያኮሩ በርካታ ገድሎችን ፈጽሟል። በ2008ቱ የቤጂንግ ኦሎምፒክ ያስመዘገበው ድል ደግሞ በጉልህ የሚነሳ ነው።
በቤጅንጉ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ አራት ወርቅ፣ ሁለት ብር እና አንድ ነሃስ በድምሩ በሰባት ሜዳልያ 17ኛ ደረጃን ይዛ ነው ያጠናቀቀችው። በወቅቱ የተገኙት አራት ወርቆች በቀነኒሳ በቀለ እና ጥሩነሽ ዲባባ ድርብ ድል አድራጊነት የተገኙ ናቸው። ሁለቱ አትሌቶች በ10 እና 5 ሺህ ሜትር በሁለቱም ርቀቶች ለሀገራቸው ወርቅ በማስገኘት በታሪክ የሚዘከር ድል ፈጽመዋል።
ቀነኒሳ በቀለ በቤጅንጉ አሎምፒክ በ10 እና 5 ሺህ ሜትር ርቀቶች ሲያሸንፍ የገባባቸው ሰዓቶች ደግሞ የኦሎምፒኩ ክብረወሰን ናቸው። ቀነኒሳ 5 ሺህ ሜትሩን 12 ደቂቃ፣ 57 ሴኮንድ ከ82 ማይክሮ ሴኮንድ በኾነ ጊዜ በመግባት አሸንፏል። ይህ ሰዓት እስካሁንም ድረስ በኦሎምፒክ የርቀቱ ክብረወሰን ነው።
በተመሳሳይ የ10 ሺህ ሜትር የኦሎምፒክ ክብረወሰን 27 ደቂቃ፣ 01 ሴኮንድ ከ 17 ማይክሮ ሴኮንድ በቀነኒሳ እጅ ይገኛል። ቢቢሲ እንደዘገበው የቤጅንግ ኦሎምፒክ ሲታወስ የቀነኒሳ እና ጥሩነሽ ድርብ ድል ቀድሞ ይመጣል። በተጨማሪ የቀነኒሳ በአንድ ኦሎምፒክ ሁለት ክብረወሰን ትልቅ ጀግንነት ኾኖ በኩራት ይወሳል።
በፓሪስ ኦሎምፒክ ቀነኒሳ በሚወዳደርበት የማራቶን ውድድር ለሀገሩ የሚያስመዘግበው ውጤት ደግሞ የሚጠበቅ ነው፡፡ በጀግናው አትሌት ቀነኒሳ እና ሌሎች አትሌቶቻችን ኢትዮጵያ የምትታወቅብትን የድል አድራጊነት ምሳሌ የኦሎምፒክ ውድድር ዘንድሮስ በፓሪሱ ድግስ ምን ውጤት ይመጣ ይሆን?
መልካም እድል ለአትሌቶቻችን!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!