ባሕር ዳር: ሐምሌ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ33ኛው የኦሎምፒክ ጨዋታዎች የ20 ኪሎ ሜትር ወንዶች የእርምጃ ውድድር ፍጻሜ ኢትዮጵያን ወክሎ የተወዳደረው አትሌት ምስጋና ዋቁማ 6ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቅቋል። በፓሪስ እየተካሄደ በሚገኘው የኦሎምፒክ ጨዋታዎች የአትሌቲክስ መርሐ ግብር ዛሬ ተጀምሯል።
ማለዳ ላይ በተደረገው የ20 ኪሎ ሜትር ወንዶች የእርምጃ ፍጻሜ ውድድር ምስጋና ዋቁማ 6ኛ ወጥቷል። አትሌት ምስጋና በመጀመሪያ የኦሎምፒክ ተሳትፎው አበረታች የሚባል ውጤት አስመዝግቧል። የእርምጃ ውድድሩ በአስቸጋሪ የአየር ፀባይ ምክንያት በ30 ደቂቃ ዘግይቶ መጀመሩን የዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ መረጃ ያመለክታል።
በውድድሩ ላይ ከ26 ሀገራት የተወጣጡ 49 አትሌቶች ተሳትፈዋል። በተያያዘም የ20 ኪሎ ሜትር ሴቶች የእርምጃ ውድድር ፍጻሜ በአስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ከተያዘለት ጊዜ 30 ደቂቃ ዘግይቶ እንደሚጀመር ታውቋል። በዚሁ መሰረት ውድድሩ ከረፋዱ 4 ሰዓት ከ50 ደቂቃ ላይ ይከናወናል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!