የአፍሪካዊያን አትሌቶች ተምሳሌቱ – አበበ ቢቂላ

0
665

ባሕር ዳር: ሐምሌ 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አበበ ቢቂላ የሚለው ስም ሲነሳ በባዶ እግሩ 42 ኪሎ ሜትር ሮጦ ማራቶንን ያሸነፈ ኢትዮጵያዊ ቆፍጣና ሰው ከፊታችን ይደቀናል፤ አበበ ቢቂላ ሲባል በቅኝ ግዛት ፈላጊዎቹ ጣሊያናዊያኑ የሮም አደባባይ ላይ የአባቶቹን የአሸናፊነት ገድል የደገመ አርበኛ ሰው ከፊታችን ይሾማል፡፡

ሻምበል አበበ ቢቂላ የተወለደው ነሐሴ 30 ቀን 1925 ዓ.ም ደነባ ልዩ ስሟ ጃቶ ከምትባል ሥፍራ ነው። በአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር 1960 በአንድ ቀን አልተገነባችም በምትባለዋ የሮም ከተማ አንድ የአርሶ አደር ልጅ በባዶ እግሩ ሮጦ ባለ ድል በመኾን ብዙዎችን አስደመመ። ለአፍሪካ አህጉርም አዲስ እና አይረሴ ታሪክ ፃፈ።

አበበ በሮም አደባባይ ላይ ማራቶንን ሲሮጥ አንድም ሰው የድሉ ባለቤት እሱ ይኾናል ብሎ አልጠበቀም፤ ይልቁንም በወቅቱ አብሮት ሲሮጥ የነበረው ሞሮኳዊው ራዲ ቤን አብዲሰላም የተሻለው ተገማች ሯጭ ነበር፡፡ ነገር ግን ሩጫው ሊጠናቀቅ አንድ ኪሎ ሜትር ገደማ ሲቀረው አበበ ቢቂላ ተቀናቃኙን ጥሎት ሽምጥ ጋለበ። የመጨረሻዎቹን ሜትሮች በአስደናቂ ፍጥነት የሮጠው አበበ እጆቹን በድል እያወናጨፈ ድሉን ለኢትዮጵያውያን፣ ለአፍሪካውያን እና ለዓለም ሕዝብ አበሰረ።

አበበ ቢቂላ በዚያች የመጀመሪያው የማራቶን ሩጫው በኦሎምፒክ መድረክ ወርቅ ያመጣ ጥቁር አፍሪካዊ ኾኖ ተመዘገበ። ይህ ብቻ ሳይኾን ውድድሩን በ2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ16 ሰከንድ በማጠናቀቅ አዲስ የኦሎምፒክ ክብረ ወሰንም በስሙ ተመዘገበ፡፡ የአቤ ድል ብዙዎችን በግርምት እጃቸውን መዳፋቸው ላይ እንዲጭኑ ያደረገ ብቻም አይደለም፤ ይልቁንም ድሉ ለብዙ ጥቁር አፍሪካዊያን የአሸናፊነት ሥነ ልቦናን ያሳደገም ጭምር ነው፡፡

አበበ ቢቂላ በወቅቱ ማንም የማያውቀው ሯጭ መኾኑ ብቻ ሳይኾን ማራቶንን በባዶ እግሩ ጀምሮ በባዶ እግሩ የጨረሰ የፕላኔታችን ብቸኛው ሰውም ኾኗል፡፡ ስለ አበበ ቢቂላ ታሪክ በመጽሐፍ ያሳተሙት እንግሊዛዊው ቲም ጁዳህ ”አበበን ከምንም በላይ በዓለም ሕዝብ ዘንድ ታዋቂ ያደረገው ኢትዮጵያዊ መኾኑ፣ ጥቁር መኾኑ ወይም አፍሪካዊ አትሌት መኾኑ ሳይኾን ማራቶንን ያሸነፈው በባዶ እግሩ መኾኑ ነው” ሲሉ በመጽሐፋቸው ከትበውለታል፡፡

አበበ ቢቂላ ከሮም ታሪካዊ ድሉ በኋላ ወደ ሀገሩ ሲመለስ የጀግና አቀባበል ተደርጎለታል። በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አደባባይ ወጥተው ተቀብለውታል። የአበበ ቢቂላ የ1960 የሮም ድል በወቅቱ በቅኝ ግዛት ለነበሩ አፍሪካዊያን ሀገራት ሁሉ የነጻነታቸው መስፈንጠሪያ፣ የአልገዛም ባይነታቸው ጅማሮ እንዲሁም የጥቁር ሕዝብ ሁሉ ክብርም ነበር፡፡

“የአፍሪካ ታሪክን ለምናውቅ ሰዎች በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ የወጡት አበበ ቢቂላ የሮም ድልን ካመጣ በኋላ ነው” የሚለው ደግሞ የቀድሞው የኦሎምፒክ እና የዓለም ሻምፒዮና የወርቅ ባለቤቱ ኢትዮጵያዊው የረዥም ርቀት ሯጭ ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ነው። አበበ ቢቂላ ከድሉ በኋላ ወደ ሀገሩ ሲመለስ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የኢትዮጵያ ኒሻን ተሸልሟል። አጼ ኃይለ ሥላሴ ከኒሻኑ በተጨማሪ የፖሊስ ማዕረግ፣ የመኖሪያ ቤት እና አዲስ መኪና ሸልመውታል።

አበበ ቢቂላ በሮም የፈጸመውን አይረሴ ጀብዱ በ1964 ቶኪዮ ላይም መድገም ችሏል። የኦሎምፒክ ማራቶንን በተከታታይ በማሸነፍ የመጀመሪያው ሰው ኾኖም ስሙ በክብር መዝገብ ላይ ሰፍሮለታል፡፡ ማራቶንን ያህል ታላቅ ውድድር ሁለት ጊዜ በማሸነፍ አበበ ቢቂላ ቀዳሚው ሰው ሲኾን ጀርመናዊው ዋልደማር ቺፒንስኪ እና ኬንያዊው ኢሊዩድ ኪፕቾጌ ደግሞ አቤን ተከትለው በኦሎምፒክ ታሪክ በተከታታይ የወርቅ ሜዳሊያ ማምጣት የቻሉ አትሌቶች ናቸው።

በነገራችን ላይ አበበ ቢቂላ በሁለተኛው የኦሎምፒክ ውድድሩ የሮጠው ጫማ ተጫምቶ መኾኑ የሚታወስ ነው። አበበ ቢቂላ ከ1960 እስከ 1966 ባለው ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካደረጋቸው 13 የማራቶን ውድድሮች 12ቱን ማሸነፍ ችሏል የሚለው የዓለም አትሌቲክስ ዘገባ አቤ ሁለተኛው የኦሎምፒክ ድሉን በቶኪዮ ካስመዘገበ ከአምስት ዓመታት በኋላ ችግር አጋጥሞታል።

መጋቢት 1969 አበበ ቢቂላ ቮክስቫገን ቢትል መኪናውን እያሽከረከረ ሳለ ባጋጠመው አደጋ ምክንያት ከአንገት በታች የሰውነት መስነፍ ‘ፓራላይዝድ’ ለመኾን ተገድዷል፡፡ ወደ እንግሊዝ ለህክምና ቢወሰድም ብርቱው ሯጭ ድጋሚ መራመድ እንደማይችል ዶክተሮቹ አረጋግጠዋል። ከጥቂት ጊዜ በኋላ አበበ እጆቹን ማንቀሳቀስ ቻለ። ይሄኔ ነው ወደ ቀስት ውርወራ እና ቴኒስ ዓይነት የስፖርት መስኮች የተሰማራው።

አበበ ቢቂላ በአውሮፓውያኑ 1973 በአደጋው ምክንያት በደረሰበት ህመም ምክንያት በ41 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በወቅቱ ብሔራዊ የሀዘን ቀን ያወጁ ሲኾን አበበ ቢቂላ በክብር እንዲቀበርም አድርገዋል። ከአበበ በኋላ የመጡ እንደ ኃይሌ ገብረሥላሴ እና ኢሊዩድ ኪፕቾጌ ያሉ ኢትዮጵያዊያን እና ኬንያዊያን ሯጮች መስኩን ተቆጣጥረውት ቆይተዋል።

“እኛ አፍሪካዊያን ሯጮች የአበበ ቢቂላ ውጤቶች ነን፤ በአበበ ቢቂላ ምክንያት እኔ ዓለም ያወቀኝ አትሌት መኾን ችያለሁ” ይላል ኃይሌ ገብረሥላሴ።

ዘጋቢ፡- እሱባለው ይርጋ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here