የፓሪስ ኦሎምፒክ የመክፈቻ ዝግጅት

0
243

ባሕር ዳር: ሐምሌ 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ ፍጹም ሰላም በኾነ መልኩ እንዲጠናቀቅ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታጠቀ የጸጥታ ኃይል በተጠንቀቅ መቆሙን ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አስታወቁ። ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት ዛሬ በይፋ በሚጀመረው ኦሎምፒክ ፈረንሳይ ለውድድሩ የሚያስፈልጉ ጉዳዮችን ሙሉ በሙሉ ማሟላቷን ነው የተናገሩት።

አንዳንድ የፓሪስ ነዋሪዎች እንግዶቹን እንዳያጨናንቁ እና የዋጋ ግሽበት እንዳይፈጥሩ በቴክኖሎጂ የታገዘ የቁጥጥር ብሎም የደኅንነት ሥራ መጀመሩን ጠቁመው ለሕገ ወጦቹ ምህረት እንደማይሰጡም ፕሬዚዳንቱ አስጠንቅቀዋል። ፕሬዚዳንት ማክሮን አክለውም ውድድሮቹ ፍጹም ሰላማዊ ኾነው እንዲጠናቀቁ በየውድድር ቦታዎች በአንድ ጊዜ እስከ 5 ሺህ የሚደርሱ ፖሊሶች፣ ወታደሮች እና ቅጥር ጠባቂዎች በመመደብ ጸጥታው በአስተማማኝ ኹኔታ ይጠብቃል ብለዋል።

የፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ፓሪስን መሃል ለመሃል ሰንጥቆ በሚያልፈው በሴይን ወንዝ ላይ እንደመደረጉ ብዙዎቹ “አረንጓዴው ኦሊምፒክ” ብለው እስከ መጥራት መድረሳቸውን ፍራንስ 24 ዘግቧል። በሥነ ስርዓቱ ላይ የጀልባ ትርኢት ይኖራል፤ ታዋቂ አትሌቶች እና ሥመ ጥር ሰዎች ይታደማሉ። 300 ሺህ ተመልካቾች ደግሞ በሴይን ወንዝ 6 ኪሎ ሜትር ርቀት በመደዳ ተሰባስበው ይታደሙበታል ነው የተባለው።

የመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ በሚከናዎንበት ወቅት ግለሰቦች በሴይን ወንዝ በኩል ለማለፍ የግድ የይለፍ መለያ (QR) ኮድ ያስፈልጋቸዋል ነው የተባለው። ይህ የፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ ሥርዓተ-ፆታን ያማካለ እንደኾነም እየተነገረ ነው። ለምሳሌም በውድድሩ 5 ሺህ 250 ወንድ እና 5 ሺህ 250 ሴት አትሌቶች ይወዳደራሉና።

ለኦሎምፒክ ዝግጅቱ ወደ 9 ቢሊዮን ዩሮ ወጭ መደረጉን ደግሞ ቢቢሲ ዘግቧል።

ዘጋቢ፡- ሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here