ባላደገው እግር ኳሳችን ላይ ያላደገው አደጋገፋችን

0
218

ባሕር ዳር: ሐምሌ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) እግር ኳስ ያለ ደጋፊዎች ምንም ነው ቢባል ስህተት አይሆንም፡፡ የኮቪድ ወረርሽኝን፣ የደጋፊዎች መቀጣት እና ሌሎች ጉዳዮችን ተከትሎ ጨዋታዎች በዝግ ስታዲየም ሲደረጉ ተመልክተናል። በዚህ መንገድ የሚደረጉ ጨዋታዎች ቅዝቃዜ ከበረዶም የባሰ መኾኑን በብዙ አጋጣሚዎች ተመልክተናል፡፡

የእግር ኳስ ደጋፊዎች ለክለባቸው ወይም ለቡድናቸው እንደ 12ኛ ተጨዋች የመቆጠራቸው ምክንያትም እግር ኳስ ያለ ደጋፊዎች የማይታሰብ የስፖርት ዓይነት ስለኾነ ነው፡፡ በሀገራችን ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ከደጋፊዎች ሥነ ምግባር ጋር በተያያዘ በስታዲየሞች ውስጥ አላስፈላጊ ነገሮችን ዓይተናል፤ የዳኞችን መደብደብ ጭምር፡፡

በቅርቡ እንኳን ለኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ የኢትዮጵያ ቡና እና የወላይታ ዲቻ ደጋፊዎች የፈጸሙትን ጥፋት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና ወላይታ ዲቻን 2 ለ 1 በረታበት በዚሁ የፍጻሜ ጨዋታ ላይ እድሳት ተደርጎለት ለመጀመሪያ ጊዜ ጨዋታ ባስተናገደው የአዲስ አበባ ስታዲየም ውስጥ በወላይታ ድቻ ደጋፊዎች 840 ወንበሮች ተሰባብረው ክለቡ 350 ሺህ ብር በቅጣት እንዲከፍል እና የወደሙ ንብረቶችንም እንዲያስጠግን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተቀጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎችም በ194 ወንበሮች ላይ ኪሣራ አድርሰው ክለባቸው 100 ሺህ ብር እንዲቀጣ እና ያወደሟቸውን ንብረቶች እንዲያስጠግን ምክንያት ኾነዋል ሲል የዘገበው ኢትዮ ሶከር ነው፡፡ ይሄንን የቅርቡን ክስተት ለአብነት አነሳን እንጂ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ላይ ጥቁር አሻራቸውን ያሳረፉ በርካታ የደጋፊዎችን ስህተቶችም መጥቀስ ይቻላል፡፡

ያም ኾኖ ግን በድጋፍ አሰጣጡ የታዩ መልካም ነገሮችንም ማንሳት ይቻላል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና ክለቦች በሚያደርጓቸው የሸገር ደርቢ ጨዋታዎች በርካታ ኅብረ ዝማሬዎችን እና የድጋፍ አሰጣጦችን ተመልክተናል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ፋሲል ከነማ፣ ባሕር ዳር ከነማ፣ ወላይታ ዲቻ፣ አዳማ ከነማ እና ሌሎችም ክለቦች በደጋፊዎቻቸው የድጋፍ ዜማ የእግር ኳስን ውብ መዝናኛነት እያሳዩን ይገኛሉ፡፡

የእግር ኳስ ውበቱም ኾነ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንትነቱ ደግሞ ደጋፊዎቹ ናቸው፡፡ እነዚሁ የእግር ኳስ ድምቀቶች የኾኑ ደጋፊዎች በአንዳንድ ስታዲየሞች ውስጥ የተሳሳተ የድጋፍ አሰጣጣቸው ለሰው ሕይዎት መጥፋት እና ለንብረት መውደም ምክንያት ሲኾኑም አስተውለናል፡፡ የባሕር ዳር ከነማ ደጋፊ እንደኾነ የገለጸልን ግዛቸው ማሩ “በእግር ኳስ ሜዳ ውስጥ ፖለቲካን ማራመድ፣ ዘረኝነትን ማንጸባረቅ እና መሰል ስድድቦች አላስፈላጊ የኾኑ ነገሮች ናቸው” ብሎናል፡፡

በእግር ኳስ መዝናናት እና የባሕል ውርርስ ማድረግ እንጂ ረብሻ እንደማይጠቅምም ነው ግዛቸው የገለጸው፡፡ የደጋፊዎች ረብሻ የሚነሳው ዳኞች በግልጽ በሚሠሩት ስህተት በመኾኑ እነሱም ስህተታቸውን ሊያርሙ ይገባልም ብሏል ግዛቸው፡፡ ሌላኛው የባሕር ዳር ከነማ ደጋፊ በረከት ሀገሩ ደግሞ “የአንድ ክለብ ደጋፊ ስትኾን መለያውን መልበስ ብቻ ሳይኾን መታወቂያ ያለህ ሕጋዊ ደጋፊ መኾን ይጠበቅብሃል” ነው ያለው፡፡ ሕጋዊ ደጋፊዎች ቢያጠፉም በሕግ የሚጠየቁበት አግባብ እንደሚኖር በመግለጽ ጭምር፡፡

በመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህሩ ሰለሞን አሳየ ደግሞ ከምንም በላይ የእግር ኳስ ደጋፊዎች ለእግር ኳሱ የጀርባ አጥንት መኾናቸውን ማመን ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡ ደጋፊዎች ከዝማሬ እና ሞራል መስጠት ባሻገር በገንዘብ ክለባቸውን የሚደግፉ እንደኾኑም አንስተዋል፡፡ የተጨዋቾች ተገቢ ያልኾነ የደስታ አገላለጽ፣ የአሠልጣኞች ስሜታዊነት፣ የዳኞች የብቃት ማነስ ወይም ኾነ ብሎ ውጤትን የመቀየር ፍላጎት እና ሌሎችም ገፊ ምክንያቶች ደጋፊዎችን ወደ ብጥብጥ የሚመሯቸው እንደኾኑም ነው መምህሩ የገለጹልን፡፡

ክለቦች ደጋፊዎቻቸውን ሕጋዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ያሉት ምሁሩ እንደ አብነት የደጋፊ ማኅበራት ደጋፊዎች ውጤትን አምነው እንዲቀበሉ ምን ሠርተዋል? ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡ የደጋፊ ማኅበራት ከደጋፊዎቻቸው ጋር መወያየት ይኖርባቸዋል፤ ማኅበራዊ ገጽ እና የትሥሥር መረቦች ሊኖሯቸውም ይገባል፤ ደጋፊዎች እንደ ተጨዋቾች ሁሉ ለእግር ኳስ የሚወጡ አዳዲስ ሕጎችን ማወቅ ይኖርባቸዋል፤ ይህ ደግሞ የዳኞችን ውሳኔ ባለማወቅ እንዳይቃወሙ ይረዳቸዋል ነው ያሉት አቶ ሰለሞን፡፡

እግር ኳስ ያለ ደጋፊ የማይታሰብ ጨዋታ ነው ያሉት መምህሩ ከነ ስህተታችንም ቢኾን የእግር ኳስ ደጋፊዎችን ከሜዳ ማራቅ አይገባም ብለዋል፡፡ የደጋፊ ማኅበራት በእግር ኳስ ሜዳ ውስጥ የሚታዩ የደጋፊ ረብሻዎችን ለማስቆም ጉልህ ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል ያሉት የስፖርት ሳይንስ መምህሩ ለአብነትም የደጋፊ ማኅበራት ጥምረት ማቋቋም፣ ከጨዋታ በፊት ለደጋፊዎች የተለያዩ መልዕክቶችን ማስተላለፍ፣ የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃንን ወይም የማኅበራዊ ትሥሥር ገጾችን በመጠቀም እግር ኳስን መዝናኛ እንጂ የብጥብጥ ማዕከል እንዳይኾን መሥራት ይቻላል ሲሉ መክረዋል፡፡

ዳኞች በሜዳ ውስጥ የሚፈጽሟቸውን የጎሉ ስህተቶች ለመቀነስ ሙያቸውን ማሻሻልና ራሳቸውን ማብቃት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በእግር ኳስ ላይ ያሉ ሁሉም አካላት በጋራ መሥራት አለባቸው፤ የምሁሩ መልዕክቶች ናቸው፡፡ በትላልቅ የእግር ኳስ መድረኮች ላይ ሳይቀር የዳኞች ስህተት ያለ በመኾኑ ደጋፊዎች ይሄንን መገንዘብ ይኖርባቸዋል ያሉት አቶ ሰለሞን ይህንን ባለመረዳት በሚያጠፉ ሕጋዊም ይሁኑ ሕጋዊ ያልኾኑ ደጋፊዎች ላይ አስተማሪ ቅጣቶች ሊጣሉባቸው ይገባልም ነው ያሉት፡፡

አሁን በኢትዮጵያ ክለቦች እና ደጋፊዎች ላይ የሚጣሉ ቅጣቶች አስተማሪ ናቸው ብለው እንደማያምኑም ጠቁመዋል፡፡ ዳኞችን የደበደቡ ተጨዋጮች እና የቡድን መሪዎች በትንሽ የገንዘብ ቅጣት የሚታለፉ ከኾነ እግር ኳሱ ውስጥ ሌሎች ከዚህ የከፉ ጥፋቶች ላላመፈጸማቸውም ዋስትና የለንም ብለዋል፡፡

እንዳለመታደል ኾኖ የኛ ሀገር ሜዳዎች የሚጠበቁት በመንግሥት የታጠቁ ኃይሎች ነው ያሉት መምህሩ በሌላው ዓለም ግን የሠለጠኑ ሥርዓት አስከባሪዎች ደጋፊዎችን ይቆጣጠራሉ ነው ያሉት፡፡ ወደፊት እግር ኳሳችን እንዲያድግ በምንፈልገው ልክ የሜዳ ላይ ሥርዓታችንም እንዲያድግ ስፖርቱ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የጋራ ርብርብ ያድርጉም ብለዋል፡፡

ባላደገው እግር ኳሳችን ላይ ያላደገ የድጋፍ አሰጣጥ ስንጨምርበት ስፖርቱን ይገድለዋል ያሉት አቶ ሰለሞን የዘርፉን ሕመም ለማከም የስፖርት ሳይንስ መምህራንን ጨምሮ ሁሉም ስፖርቱ የሚመለከተው አካል መምከር እና የተግባር ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅብናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here