ባሕር ዳር: ሐምሌ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጀርመን የደገሰችው የ2024 የአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜውን ሊያገኝ ቀናት ቀርተውታል፡፡ ስፔን እና እንግሊዝ የሚያደርጉት የፍጻሜ ጨዋታ ደግሞ ተጠባቂ ኾኗል፡፡
በውድድሩ ሁሉንም በማሸነፍ ድንቅ ብቃቷን ያሳየችው ስፔን ዋንጫውን ከፍ ታደርገው ይኾን? ወይንስ በበርካታ ከዋክብት የተመላቸው እና በውድድሩ ማራኪ እግር ኳስ እንቅስቃሴ ሳታሳይ ለፍጻሜ የደረሰችው እንግሊዝ ከፍ ታደርገዋለች? የሚለው የእግር ኳስ አፍቃሪያንን ቀልብ ይዟል፡፡ ዋንጫውን ከፍ ከሚያደርገው ብሔራዊ ቡድን ባለፈ የውድድሩ ኮኮብ ተጨዋች፣ የውድድሩ ኮኮብ ግብ አግቢ፣ የውድድሩ መርጡ ግብ ጠባቂ እና የውድድሩ ምርጥ ታዳጊ ተጨዋች እነማን ይኾኑ የሚለው በጉጉት ይጠበቃል፡፡
በውድድሩ ስድስት ተጨዋቾች ሦስት ሦስት ግቦችን በማስቆጠር በእኩል እየመሩ ነው፡፡ የቢቢሲ ዘገባ እንደሚያመላክተው ከስፔን ብሔራዊ ቡድን ጋር ለፍጻሜ የደረሰው ዳኒ ኦልሞ ፣ ከእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ጋር ለፍጻሜ የደረሰው ሀሪ ኬን፣ ጆርጂያዊ ጆርጂስ ሚካታድዜ፣ ኔዘርላንዳዊ ኮዲ ጋክፖ፣ ስሎቫኪያዊ ኢቫን ሻርንዝ እና ጀርመናዊ ጀማል ሙሲያላ ተመሳሳይ ሦስት ግቦችን አስቆጥረዋል፡፡
ስፔናዊ ዳኒ ኦልሞ ሦስት ግብ ከማስቆጠር ባለፈ ሁለት ግቦችን አመቻችቶ በማቀበል ቀዳሚው ተጨዋች ነው፡፡ ጆርጂያዊ ጆርጂስ ሚካታድዜ እና ኔዘርላንዳዊ ኮዲ ጋክፖም ሦስት ሦስት ግቦችን ከማስቆጠር ባለፈ በተመሳሳይ አንድ አንድ ግብ አመቻችተው አቀብለዋል፡፡ ከሥድስቱ ተጨዋች መካከል ጥቂት ጨዋታዎችን ያደረጉት ደግሞ ጆርጂያዊ ጆርጂስ ሚካታድዜ እና ስሎቫኪያዊ ኢቫን ሻርንዝ ናቸው፡፡ ሁለቱ ተጨዋቾች በአራት ጨዋታዎች ነው ሦስት ሦስት ግቦችን ያስቆጠሩት፡፡ ሌሎቹ ተጨዋች ከእነርሱ የበለጠ ጨዋታዎችን አድርገዋል፡፡
ስፔናዊያኑ ዳኒ ኦልሞ እና እንግሊዛዊው ሀሪ ኬን የፍጻሜው ጨዋታ እድል ስላላቸው ግብ ያስቆጠረ ተጨዋች ኮኮብ ግብ አግቢነቱን ለብቻው መምራት የሚችልበት እድል አለ፡፡ ጊቭ ሚ ስፖርት የተሰኘው ድረ ገጽ በውድድሩ ዋንጫውን ከማሸነፍ በሻገር የወርቅ ጫማውን መውሰድ አንድ ተጨዋች ከሚያገኛቸው እርካታዎች እና ስኬቶች መካከል አንደኛው ነው ይላል፡፡ የወርቅ ጫማው ተጨዋቹ በውድድሩ ላይ ያሳየውን ድንቅ ብቃት ያሳየበት ሽልማት ስለሚኾን ለተጨዋቾች ልዩ ትርጉም አለው፡፡ የወርቅ ጫማውን ለመውሰድ የመዲረገው ፉክክርም ከባድ መኾኑን ያነሳል፡፡
አንዳንድ ጊዜ በአንድ ውድድር ላይ በርካታ ተጨዋቾች ብዙ ግቦችን ያስቆጥራሉ የሚለው ጊቭ ሚ ስፖርት የ2024 የአውሮፓ ዋንጫ ከእንደዚህ አይነት አጋጣሚዎች መካከል አንደኛው ነው ይላል፡፡ ተጨዋቾች ተመሳሳይ ግብ ሲያስቆጥሩ ለሁሉም ይሰጣል ወይስ ለየትኛው ተጨዋች የወርቅ ጫማው ይሰጣል ? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡ ጊቭ ሚ ስፖርት እንደሚለው ተመሳሳይ ግቦችን ያስቆጠሩ ተጨዋቾች ከበዙ በውድድሩ ለግብ አመቻችተው ያቀበሉት ኳስ ይታያል፡፡
ሁሉም ተጨዋቾች ተመሳሳይ ግብ ካስቆጠሩ እና ተመሳሳይ ኳስ አመቻችተው ካቀበሉ ደግሞ ሌላ መለያ ይታያል፡፡ ተጨዋቾችን ለመለየት ጥቂት ደቂቃዎችን የተጫወተ እና በጥቂት ደቂቃዎች ብዙ ግቦችን ያስቆጠረው የትኛው ተጫዋች ነው በሚለው ይለያሉ፡፡ በዚህ ስሌት ሲታይ ስፔናዊው ዳኒ ኦልሞ የወርቅ ጫማውን የማግኘት እድሉ ሰፊ ነው ይላል ዘገባው፡፡ ነገር ግን እንግሊዝ እና ስፔን በፍጻሜው ጨዋታ ስለሚገናኙ ነገሮች ሊለወጡ እንደሚችል ነው የሚያመላክተው፡፡
በፍጻሜው ጨዋታ የአውሮፓ ዋንጫ ወደ ለንደን ወይስ ወደ ማደሪድ ይሄዳል? የሚለው በጉጉት ይጠበቃል፡፡ በተከታታይ ለፍጻሜ የደረሰው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ዋንጫውን ይዞ ወደ ለንደን የሚመለስ ከኾነ አዲስ ታሪክ ይጽፋል፡፡ የውድድሩ አስደናቂ ቡድን የስፔን ብሔራዊ ቡድን ደግሞ ዋንጫውን ይዞ ወደ ማደሪድ የሚያቀና ከኾነ ከ12 ዓመታት በኋላ የሚበረከት ሌላኛው ስጦታ ይኾናል፡፡ የስፔን ብሔራዊ ቡድን ከአስራ ሁለት ዓመታት በፊት የአውሮፓ ዋንጫ ከፍ አድርጓልና፡፡
ዳኒ ኦልሞ ወይስ ሀሪ ኬን የወርቅ ጫማውን ይወስዳሉ? የሚለውም ከዋንጫው ባሻገር ይጠበቃል፡፡ እንደ ጊቭ ሚ ስፖርት ዘገባ ከኾነ የወርቅ ጫማውን ለመውሰድ የሚፎካከሩት አነርሱ ብቻ አይደሉም፡፡ ሁለት ግቦችን ያስቆጠረው እንግሊዛዊ ጁድ ቢሊንግሃም በፍጻሜው ጨዋታ በአስደናቂ ብቃት ሁለት ግቦችን ካስቆጠረ የወርቅ ጫማውን ሊወስድ ይችላል ነው የተባለው፡፡
በተመሳሳይ ሁለት ግቦች ያሉት ስፔናዊው ፋቢያን ሩዝ በፍጻሜው ጨዋታ ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ከቻለ የወርቅ ጫመውን ሊወስድ ይችላል ይላል፡፡ ፋቢያን ሩዝ ሁለት ግቦችን ከማስቆጠር ባለፈ ሁለት ግቦችን አመቻችቶ አቀብሏል፡፡ እሁድ በጀርመኗ ርዕሰ መዲና በርሊን የሚደረገው ጨዋታ ግምቶችን፣ ምኞቶችን እና ተስፋዎችን ወደ እውነታዎች ይቀይራል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!