ባሕር ዳር: ሐምሌ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የ2024 የጀርመኑ የአውሮፓ ዋንጫ እያጓጓ ቀጥሏል። በውድድሩ መቶ በመቶ የማሸነፍ ክብረወሰኑን ያስጠበቀው የስፔን ብሔራዊ ቡድን ትናንት ምሽት በተደረገ ጨዋታ ፈረንሳይን በማሸነፍ ለፍጻሜ ደርሷል። የስፔን ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ምሽት በሚደረገው ጨዋታ የፍጻሜ ተጋጣሚውን ያውቃል።
ዛሬ ምሽት 4 ሰዓት ላይ በጀርመኑ የአውሮፓ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ኔዘርላንድስ እና እንግሊዝ አጓጊውን ፍልሚያ ያደርጋሉ፡፡ በአስደናቂ የብቃት ደረጃ ላይ የምትገኘው ስፔን ፈረንሳይን 2 ለ 1 በኾነ ውጤት አሸንፋ ለዋንጫው ፍልሚያ የኔዘርላንድስን እና የእንግሊዝን አሸናፊ በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች፡፡
እንግሊዝ እና ኔዘርላንድስ 4 ጊዜ በነጥብ ጨዋታዎች ተገናኝተዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1988 በአውሮፓ ዋንጫ ብርቱካናማዎቹ ሦስቱ አናብስትን 3 ለ 1 በኾነ ውጤት ረትተዋል፡፡በወቅቱ ሦስቱንም የኔዘርላንድስ ግቦች ያስቆጠረው ደግሞ ስመ ጥሩ ሆላንዳዊ አጥቂ ማርኮ ቫን ባስተን መኾኑን የስካይ ስፖርት መረጃ ያመለክታል፡፡
በ1990 በዓለም ዋንጫው የተገናኙት ሁለቱ ሀገራት ጨዋታቸውን ያለ ግብ በአቻ ውጤት አጠናቅቀዋል፡፡ በ1996 የአውሮፓ ዋንጫ ጨዋታ ደግሞ እንግሊዝ ኔዘርላንድስን 4 ለ 1 በኾነ ውጤት አሸንፋታለች፡፡ ኔዘርላንድስ እና እንግሊዝ በቅርብ ባደረጓቸው ዘጠኝ የእርስ በርስ ጨዋታዎች እንግሊዝ ማሸነፍ የቻለችው በአንዱ ብቻ ነው፡፡ በአራቱ አቻ ወጥተው በአራቱ ደግሞ ተሸንፋለች፡፡
የእንግሊዝ የአሸናፊነት ድል የተመዘገበው በ2018 በአምስተርዳም ስታዲየም ባደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ ነው፡፡ የኔዘርላንድሱ የፊት መስመር ተሰላፊው ሜምፊስ ዴፓይ በአውሮፓ ዋንጫው 17 የግብ ሙከራዎችን ያደረገ ሲኾን ኮዲ ጋክፖ ደግሞ 13 የግብ ሙከራዎችን እና ሦስት ግቦችን ለሀገሩ አስመዝግቧል፡፡
በእንግሊዝ በኩል የፊት መስመር ተሰላፊዎቹ ሀሪ ኬን፣ ጁዲ ቤሊንግሃም እና ፊል ፎደን እስካሁን በተጠበቁት ልክ ሀገራቸውን እያገለገሉ አይደለም በሚል በስፖርት ተንታኞች እየተተቹ ነው። በዛሬ ምሽቱ ጨዋታ የሁለቱም ሀገራት አሠልጣኞች አሸንፈው ለፍጻሜው ጨዋታ እንደሚቀርቡ ለቢቢሲ ከሰጡት መረጃ መረዳት ይቻላል፡፡
የአውሮፓ ዋንጫን በታሪኳ አሸንፋ የማታውቀው እንግሊዝ በ2020 የአውሮፓ ዋንጫ በፍጻሜው በጣሊያን ተሸንፋ ዋንጫውን ተነጥቃለች። ወደ ጀርመን ከማቅናቱ አስቀድሞ ዋንጫውን ለማሸነፍ ቅድሚያ ግምት የተሰጠው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን በተከታታይ ለፍጻሜ ለመድረስ ይጫወታል። እንደ ቨርጅል ቫንዳይክ፣ ናታን አኬ፣ ኮዲ ጋክፖ እና ሌሎች ከዋክብትን የያዘው የኔዘርላንድስ ብሔራዊ ቡድን የእንግሊዝ ብርቱ ተፎካካሪ እንደሚኾን ይጠብቃል። የዛሬውን ጨዋታ አሸንፎ ለፍጻሜ የሚበቃው ሀገር ማን ይኾን? ምሽት አራት ሰዓት በዶርትመንድ የመጫወቻ ሜዳ ሲግናል ኢዱና ፓርክ የሚደረገው ጨዋታ ምላሽ ይኖረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!