ባሕር ዳር: ሀምሌ 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አፍሪካውያን በነፃነት፣ በአንድነት፣ በጀግንነት፣ በጥንታዊነት፣ በራስ መልክ እና ማንነት አርዓያ የሚያደርጓት፣ ተስፋ ባጡ ዘመን ተስፋ ኾና ያገኟት፣ በጨለማ ዘመን እንደብርሃን ኾና የተመለከቷት፣ የዘመን መብራት፣ የእናነትነት ምሳሌ ናት።
የቅኝ ግዛት እጆች በረዘሙበት፣ አፍሪካዊያን በቅኝ ገዢዎች መንጋጋ ውስጥ በገቡበት፣ በአራቱም አውታር በጦር በተወጠሩበት፣ ነፃነታቸውን፣ ማንነታቸውን፣ ባሕልና ታሪካቸውን፣ ሃይማኖት እና እሴታቸውን፣ ወግና ልማዳቸውን በተነጠቁበት ዘመን ነፃነቷን አስጠብቃ፣ ወሰኖቿን አጥብቃ፣ በጨለማ አሕጉር ብቻዋን ደምቃ ትኖር ነበር።
ፍትሕ ለተጓደለባት ዓለም የፍትሕ ሚዛን የኾነች፣ ለቅኝ ተገዢዎችም ለቀኝ ገዢዎችም ያስደነቀች ሀገር ናት- ኢትዮጵያ። የዓለም መንግሥታት በጋራ የመሠረቱትን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ከአፍሪካ ቀድማ የመሠረተች፣ በቅኝ ግዛት የተከፋፈሉትን አፍሪካውያንን በአንድነት ለማስተሳሰር የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ያቆመች ሀገር ናት። ይህን ሁሉ አድርጋ በስፖርቱ ዘርፍም አፍሪካውያን በዓለም ፊት ራሳቸውን የሚያሳዩበት፣ ራሳቸው ደግሰው ራሳቸው የሚታደሙበት የእግርኳስ ውድድር ይኖራቸው ዘንድ የአፍሪካ ዋንጫን የመሠረተች ለእልፍ ነገር ቀዳሚ የኾነች፣ ብዙዎችን መንገድ የመራች ሀገር ናት ኢትዮጵያ።
አፍሪካውያን የሚሳተፉበትን፣ ባሕልና ወጋቸውን፣ ታሪክና ማንነታቸውን የሚገልጹበትን የአፍሪካን ዋንጫን የመሠረተችው ኢትዮጵያ በአፍሪካ እግር ኳስ ታሪክ ወርቅ ያቀለመው ታሪክ አላት። በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን የአፍሪካ ዋንጫን የመሠረተችው ሀገር ተጫዋቾች በንጉሣቸው ፊት የአህጉሪቱን ዋንጫ ከፍ አድርገው ታሪክ ጽፈዋል። ንጉሣቸውን አኩርተዋል፤ የሀገራቸውን ሠንደቅ ከፍ አድርገው አውለብልበዋል፤ ለኢትዮጵያውያንም የደስታ ስጦታ ሰጥተዋል። ታዲያ ለአፍሪካ በብዙ ነገር ምሳሌ የኾነች እና የአፍሪካ ዋንጫን የመሠረተች ሀገር ኢትዮጵያ መሠረቱን ባስቀመጠችው ቤቷ መድቀመቅ ከተሳናት ዓመታት ተቆጥረዋል።
ለአፍሪካ መንገዱን ያሳየችው ሀገር በንጉሣቸው ፊት ዋንጫውን ከፍ አድርገው፣ ሠንደቃቸውን እያውለበለቡ እንደጀገኑት ዓይነት ተጫዋቾችን አጥታ ቀዳሚ የነበረችው ሀገር የበይ ተመልካች ኾናለች። በመሠረተችው የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ ተቸግራለች። ከ31 ዓመታት እና ከ8 ዓመታት በኋላ ተፍጨርጭራ ብትሳተፍም ያለ ጥሩ ውጤት ትመለሳለች። እግር ኳስን አብዝተው የሚወዱት ኢትዮጵያውያንም የኳስ ፍቅራቸውን የሚያረካ ብሔራዊ ቡድን አጥተዋል። በአፍሪካ እግር ኳስ ታሪክ ስም በሌላቸው ሀገራት ጭምር ትፈተናለች፤ ትሸነፋለች፡፡
የአፍሪካ ዋንጫን የመሠረተች ሀገር ከፍ ማለት ሲገባት ስለ ምን ዝቅ እያለች ሄደች? በባሕርዳር ዪኒቨርሲቲ ስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል የእግር ኳስ አሠልጣኝነት መምህር ኃይለኢየሱስ ባዘዘው (ዶ.ር) የአፍሪካ ዋንጫን የመሠረተች ሀገር ከፍ ማለት ሲገባት ስለ ምን ዝቅ እያለች ሄደች? የሚለው ጥያቄ የኢትዮጵያውያን ጥያቄ እና ቁጭት ነው፡፡ ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የተመለስንበት ዘመን ወደ ከፍታችን እየተመለስን የነበረበት ነው ይላሉ፡፡
በ1990ዎቹ ተጀምሮ የነበረው የእግር ኳስ ሥልጠና ፕሮጄክት እና የፕሮጄክት ውድድር የተሠራው ሥራ ታዳጊዎችን ለብሔራዊ ቡድን አብቅቷቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ የዚያ ፕሮጄክት ውጤት ታዳጊዎቹም ኢትዮጵያን ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ እንድትመለስ እንዳደረጉ ነው የተናገሩት፡፡ ተስፋ ያሳየው ፕሮጄክት የተሰጠው ትኩረት በመቀነሱ ለብሔራዊ ቡድን የነበረውን መመጋገብ ቀነሰ፤ እነ አዳነ ግርማ፣ ደጉ ደበበ፣ አበባው ቡጣቆ፣ ሰላሃዲን ሰዒድ እና ሌሎች ተጫዋቾች የወጡት ከዚያ ፕሮጄክት ነበር ነው የሚሉት፡፡ የፕሮጄክት መዳከም እና መጥፋት ተመጋጋቢ እግር ኳስ እንዳይኖር አደረገ፡፡ ይህ ደግሞ ብሔራዊ ቡድኑን ጎዳው፡፡
ክለቦችም ቢ ቡድናቸውን ለይስሙላ ይዘው ያሠለጥናሉ እንጂ ዋናውን ቡድናቸውን እና ብሔራዊ ቡድኑን ሊያግዝ የሚችል ሥልጠና እየተሰጠ አይደለም ነው የሚሉት፡፡ ይህ በመኾኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሕዝቡ በሚፈልገው ልክ መኾን ተሳነው፡፡ ታዳጊዎች ላይ መሠረት ያደረገ ሥልጠና እየተሰጠ ባለመኾኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጋሽ ሰውነት የአሠልጣኝነት ዘመን ብልጭ ብሎ ጠፋ፡፡ ይህ ደግሞ ሁላችንም አንገት የሚያስደፋ ኾነ ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ከመመሥረት አልፋ ዋንጫውን ማንሳቱን የሚያነሱት መምህሩ በወቅቱ የተሳተፉት አራት ሀገራት መኾናቸውን ዋንጫ ለማንሳት መልካም አጋጣሚ ኾኖ ሊነሳ ይችላል፤ ነገር ግን የተሻለ ብሔራዊ ቡድን ይዘን ስለቀረብን ዋንጫ አንስተናል፤ ዋጋውን የምናሳጣው አይኾንም፤ በእግር ኳስ የምትፈራ እና የምትከበር ሀገርም ነበረች ነው የሚሉት፡፡ በዚያ ወቅት በየጠቅላይ ግዛቶቹ ተሰጥኦ የነበራቸው ተጫዋቾች ነበሩ፣ ተጨዋቾች የሚመለመሉትም በየጠቅላይ ግዛቶቹ ውድድሮች ተደርገው ነበር፡፡ እግር ኳስን በፍላጎት የሚጫወቱ ወጣቶች የበዙበት ዘመንም ነበር ነው የሚሉት መምህሩ፡፡
አሁን ላይ ግን እግር ኳስን በፍላጎት ከመጫወት ይልቅ ገንዘብን መሠረት አድርጎ መጫወት ኾነ፡፡ አሁን ያሉ ተጫዋቾች ትኩረታቸው ውጫዊ በኾነው ጉዳይ ነው፤ የቀደሙት ተጫዋቾች ግን ፍላጎትን መሠረት አድርገው ሀገርን፣ የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማን ከፍ አድርጎ ማሳየትን የሚጓጉ ስለነበሩ መልካም ጊዜ ነበር፡፡ የብሔራዊ ቡድኑን ውጤት ማጣት በአሠልጣኙ ላይ ብቻ መጣል ተገቢ አይደለም፣ የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ከታች ጀምረው በጥራት እየሠለጠኑ የመጡ ተጫዋቾች ያስፈልጉታል፡፡ በየክለቦች የሚገኙ አሠልጣኞች ጊዜያዊ ውጤትን ታሳቢ ያደረገ እንጂ ብሔራዊ ቡድኑን አስበው እንደማያሠለጥኑም ተናግረዋል፡፡
የክለብ አሠልጣኞች ለብሔራዊ ቡድን ብቁ ተጫዋቾችን የማፍራት ሀገራዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው መረዳት አለባቸው ነው የሚሉት፡፡ ተጫዋቾች ብሔራዊ ቡድን ታሳቢ ያደረገ ሥልጠና ስለማይሰጡ ወደ ብሔራዊ ቡድኑ ሲመጡ ውጤታማ አይኾኑም፤ ለብሔራዊ ቡድኑም አሉታዊ ተጽዕኖ አለው፤ አሠልጣኙም በሚፈልገው መልኩ ለማጫወት ይቸገራል፤ ይሄም የብሔራዊ ቡድኑ ውጤት እንዲያሽቆለቁል አድርጓል ነው ያሉት፡፡ የክለብ አሠልጣኞች የአሠለጣጠን ዘዴም ተጫዋቾችን የሚያሳድግ አለመኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ የእኛ ሀገር ተጫዋቾች ወደ ሥልጠና መጥተው መሐል በገባ ተጫውተው፣ ኳስ አንቀርቅበው ተመልሰው አብዛኛውን ጊዜ የሚያሳልፉት ማኀበራዊ ሚዲያ እና ቤታቸው ውስጥ ነው ይላሉ፡፡ እግር ኳሳቸው ባደጉ ሀገራት ግን የተጫዋቾችን ብቃት የሚያሳድግ ልዩ ልዩ ሥልጠና ይሰጣቸዋል ብለዋል፡፡
እንደ መምህሩ ገለጻ እግር ኳስ የቡድን ሥራ በመኾኑ የአንደኛው ተጨዋች ድክመት ብሔራዊ ቡድኑን ይጎደዋል፤ ሁሉም ተጫዋቾች እግር ኳሱ ለሚጠይቀው ሥነ ምግባር እና ግዴታ ተገዢ መኾን ይጠበቅባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስኬታማ እንዲኾን ያለው የመፍትሔ ሐሳብ ምንድን ነው ?
የመጀመሪያው የመፍትሔ እርምጃ ታዳጊዎች ላይ መሥራት ነው፡፡ እግር ኳሱን የሚመሩ መሪዎች እግር ኳስን ለማሳደግ ታዳጊዎች ላይ መሥራት ይገባል ይላሉ፤ ነገር ግን ሲተገብሩ አይታይም፡፡ ለውጥ የሚያመጣው የተግባሩ ሥራ ነው ብለዋል፡፡ ወጣቶች ላይ መሥራትን ከመናገር ይልቅ ሠርቶ ማሳየት ቀዳሚው መፍትሔ ነው፡፡
በየክለቦች የሚያሠለጥኑ አሠልጣኞች አቅም፣ ብቃት እና ጥራት ያላቸው ሊኾን ይገባል፤ ለተጫዋቾች ጥራት ያለው ሥልጠና የሚሰጡ አሠልጣኞች ካሉ እግር ኳሱ ላይ ለውጥ ይመጣል ነው የሚሉት፡፡ አሠልጣኞችም አቅማቸውን የሚያሳድጉ ሥልጠናዎች እንዲሰጣቸው ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡ የእግር ኳስ ሜዳን የተሟላ ማድረግ ሌላኛው መፍትሔ መኾኑን ነው ያነሱት፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሜዳው እየተጫወተ አለመኾኑ በእጅጉ ጎድቶታል፤ በሜዳ መጫወት በአየር ንብረት፣ በደጋፊ እና በሌሎች እድሎች እንዲበልጥ ያደርጋል፡፡ ይህን አለማድረግ ግን በሜዳ ላይ የሚገኘውን እድል ያሳጣል፤ ውጤትም ያሳጣል ነው ያሉት፡፡
ተሰጥኦ ያላቸው ተጫዋቾች የሚገኙባቸው አካባቢዎችን መምረጥም ይገባል ብለዋል መምህሩ፡፡ በጥናት የተመሠረተ አካባቢዎችን በመለየት ታዳጊዎች ላይ ከተሠራ ብሔራዊ ቡድኑ የተሻለ እንደሚኾንም ገልጸዋል፡፡ ለተጨዋቾች ተነሳሽነትን የሚጨምሩ ሥልጠናዎች መስጠት ይገባል የሚሉት መምህሩ ሀገራዊ ፍላጎት እንዲኖራቸው፣ ለሠንደቅ ክብር እንዲዋደቁ፣ ከእግር ኳስ በላይ የሀገር ክብር ይዘው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ የሚያስገነዝብ ሥልጠና መስጠት ይገባል ይላሉ፡፡
በሀገራት ጨዋታ ሽንፈት ሞት እንደኾነ የሚቆጥሩ የሌሎች ሀገራት ተጫዋቾች አሉ፤ በእኛ ሀገር ግን መሸነፍ ልማድ እየኾነ፣ የመሸነፍ ሥነ ልቦና የያዘ ተጫዋች የበዛበት ኾኗል ነው የሚሉት፡፡ መለያውን መልበስ፣ ከመለያው ባሻገር ሀገር የሚለውን ክብር የቀነሰበት ተጫዋች አለ፤ በዛው ልክ ደግሞ ስለ ሀገር የሚዋደቁ፣ የሀገር ክብር የሚያንገባግባቸው ተጨዋቾችም አሉ ብለዋል፡፡
የሕዝቡን ያክል የሚቆጩ፣ የማሸነፍ ታጋይነታቸው፣ ለክብር የመዋደቅ ወኔያቸው ከፍ ያለ ተጨዋቾችን ለማየት በሥነ ልቦና የታገዘ ሥልጠና እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡ እግር ኳስን የሚያውቁ ባለሙያችን በማሰባሰብ እግር ኳሱ ከፍ የሚልበትን ሥራ መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!