ባሕር ዳር: ሐምሌ 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በጦርነት ቀውስ ውስጥ በምትገኘው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምሥራቃዊ ክፍል በምትገኘው ጎማ መንደር የጎዳና ልጆችን በሚደግፍ የቦክስ (ቡጢ) ማዕከል ውስጥ ታዳጊዎች የቦክስ ሥልጠና እየወሰዱ ነው። ናይማ ቦክሲንግ ማዕከል ጌል አሱማኒ በሚባል ሰው በጎማ ግዛት እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በ2020 የተመሰረተ ነው።
አሱማኒ በ2020 እና በ2021 የዴሞክራቲክ ኮንጎ የቀላል ሚዛን የቦክስ ሻምፒዮን ነው ። አሱማኒ ሲናገር ለሥልጠና የሚመጡ ልጆች ሁለት ዓይነት ናቸው ይላል። ከወላጆቻቸው ጋር እየኖሩ ድህነት ከብዷቸው ወደ ጎዳና የወጡ እና በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ተፈናቅለው የመጡ ናቸው ።
እነዚህን ተስፋ የራቃቸው ልጆች በማሠልጠን ተስፋ እንደሚሰጧቸው እና ቤተሰብ እንዳላቸው እንዲያስቡ እንደሚያግዟቸው ይናገራል። አሱማኒ ስፖርት ከጎዳና ሕይወት እንዲወጣ እንዳገዘው እና ሌሎች ተጋላጭ የኾኑትንም ለመርዳት ፍላጐት እንዳለው ይናገራል። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1990 ቤተሰቦቹ እንደ አብዛኞቹ የጎማ ነዋሪዎች በሥደት ወደዚህ መምጣታቸውን፣ ለ5 ወር በካምፕ ማሳለፉን እና ገና በ10 ዓመቱ እናቱን በወሊድ ወቅት ባጋጠማት ችግር በሞት ካጣ በኋላ ወደ ጎዳና ወጥቶ እንደነበረም ገልጿል ።
በጎማ ጦርነትን ፈርተው የተፈናቀሉ ልጆች አብዛኞቹ ለጎዳና ተዳዳሪነት የሚጋለጡ ሲኾን አሱማኒ ባስጀመረው ሥልጠና ከ100 በላይ ታዳጊዎች እየሠለጠኑ ይገኛሉ፤ ሲል አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል፡፡ በኛስ ሀገር ለጎዳና ሕይወት ተጋላጭ የኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን እንደ አሱማኒ በጥቂቱም ቢኾን ለመርዳት ምን ማድረግ ይኖርብናል? የስፖርትም ኾነ ሌላ ሙያ ባለቤቶች እና ባለሃብቶችስ ከአሱማኒ ምን ሊማሩ ይችላሉ?
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!